መንግሥት በትግራይ ክልል ያለው ግጭት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ቁርጠኝነቱን በተደጋጋሚ አሳይቷል - ኢዜአ አማርኛ
መንግሥት በትግራይ ክልል ያለው ግጭት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ቁርጠኝነቱን በተደጋጋሚ አሳይቷል
ጥቅምት 09 ቀን 2015 (ኢዜአ) መንግሥት በትግራይ ክልል ያለውን ግጭት በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር በሚደረጉ የሰላም ውይይቶች ለመፍታት እንደሚፈልግ በተደጋጋሚ ባደረጋቸው ጥረቶች ቁርጠኝነቱን አሳይቷል ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና ሶሻል አንትሮፖለጂስት ከይረዲን ተዘራ ገለጹ ።
ከይረዲን ተዘራ(ዶ/ር) በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክቶ ከአልጀዚራ የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
መንግሥት በትግራይ ክልል ያለውን ግጭት በሰለማዊ መንገድ ለመፍታት ተደጋጋሚ ጥረቶችን ሲያደርግ መቆየቱን የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊገነዘብ ይገባል ብለዋል።
በክልሉ እየተካሄደ በሚገኘው ግጭት ዙሪያ ጥናት ማድረጋቸውን ጠቅሰው አለም አቀፉ ምህበረሰብ በክልሉ ጦርነትን ያወጀው እና አለመረጋጋትን ለማስቀጠል እየሰራ የሚገኘው የህወሃት ቡድን መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል ብለዋል።
መንግስት ግጭቱን በማስቆም የተናጥል የተኩስ አቁም በማድረግ የሰበአዊ እርዳታ ተደራሽ እንዲሆን ቢሰራም አሸባሪው ሕወሓት ግን የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ወደ ጎን በመግፋት ባለፈው ነሐሴ ወር ለሶስተኛ ግዜ ጦርነት መክፈቱን አስታውሰዋል።
አሸባሪው ቡድን ወደ አጎራባች ክልሎች ወረራ በሚፈጽምበት ወቅት መንግሥት የዜጎቹን ደህንነት የመጠበቅና የሀገሪቱን ሉአላዊነት የማስጠበቅ ግዴታውን አለም አቀፉ ማህበረሰብ በአግባቡ መረዳት እንዳለበት ገልጸው መንግስት ግጭቱ ሊያበቃ የሚችልባቸውን የሰላም አማራጮች ሁሉ ለመጠቀም ዝግጁ መሆኑን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ትግራይ ክልልን ብቻ ሳይሆን መላ ኢትዮጵያን የማስተዳደር ሕገ መንግስታዊ ሃላፊነት ያለው ሕጋዊ አካል መሆኑን ጠቅሰው በክልሉ የሚገኙ የተወሰኑ ቦታዎችን መቆጣጠሩ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ለማስጠበቅ እና በክልሉ የሰበአዊ እርዳታ ተደራሽ ለማድረግ መሆኑን መታወቅ አለበት ብለዋል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የተወሰኑ የትግራይ ክልል ከተሞችን መቆጣጠሩን መግለጹ የሚታወስ ነው።