የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ከዩናይትድ ኪንግደም የልማት ሚኒስትር ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ከዩናይትድ ኪንግደም የልማት ሚኒስትር ጋር ተወያዩ
ጥቅምት 9/2015 /ኢዜአ/ ከዓለም ባንክ እና ከአይኤምኤፍ ጉባኤ ጎን ለጎን የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ከዩናይትድ ኪንግደም የልማት ሚኒስትር ቪኪ ፎርድ ጋር በአሜሪካ ተወያዩ።
በአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና የአለም ባንክ ዓመታዊ ጉበኤ ላይ በመሳተፍ ላይ የሚገኙት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ከስብሰባው ጎን ለጎን ከዩናይትድ ኪንግደም የልማት ሚኒስትር ቪኪ ፎርድ ጋር ተወያይተዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ስለሚገኘው የኢኮኖሚ ሪፎርም፣የሰላም ሂደት፣ እያጋጠሙ ስለሚገኙ ፈተናዎችና በኢኮኖሚው ላይ ባመጣው ተጽኖ ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በኢትዮጵያ እየተተገበረ የሚገኘውን ሪፎርም ውጤታማ ለማድረግ እና ሀገሪቱ እያጋጠሟት የሚገኙትን ፈተናዎች ለመቅረፍ ከአለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት፣የሁለትዮሽ ድርጅቶች ፤ ከአለም አቀፍ የልማት አጋሮች ስለሚያስፈልግ ትብብር ውይይት አድርገዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም የልማት ሚኒስትር ቪኪ ፎርድ በኢትዮጵያ እየተካሄደ የሚገኘውን ሪፎርም አድንቀው መንግሥት የጀመረውን የሰላም ሂደት እንደሚደግፉ አስታውቀዋል።
በተጨማሪም ሚኒስትሯ ዩናይትድ ኪንግደም ለኢትዮጵያ ስታደርግ የቆየችውን ድጋፍ እንደምትቀጥል መግለጻቸውን በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኢምባሲ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ያወጣው መረጃ ያመላክታል።