ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ኮላ እና የእጅ ሎሽን ምርት ግብዓት የሚሆን "ጀላቲን" የተባለ ምርት በመላክ የውጭ ምንዛሬ አገኘች

174

ጥቅምት 8/2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ኮላና እና የእጅ ሎሽንን ለማምረት ግብዓት የሚሆነውን "ጀላቲን" የተባለ ምርት በመላክ የውጭ ምንዛሬ ማግኘቷን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሚኒስቴሩ የስራ ኃላፊዎችና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ለኮላና የእጅ ሎሽን ግብዓት የሚሆን "ጀላቲን" የተባለ ምርት የሚያመርተውን ጂንሲንግ ጃንግ ፋብሪካ ጎብኝተዋል።

ፋብሪካው በሞጆ ከተማ የሚገኝ ሲሆን ምርቱን ለማምረት የቆዳ ተረፈ ምርቶችን የሚጠቀም መሆኑን የፋብሪካው የሥራ እንቅስቃሴ በተጎበኘበት ወቅት ተገልጿል።  

ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት ለ200 ኢትዮጵያዊያን የሥራ እድል የፈጠረ ሲሆን ምርቱ በአሁኑ ወቅት በዋናነት ወደ ቻይና እየተላከ በውጭ ምንዛሬ ግኝት የድርሻውን እያበረከተ መሆኑ ተመላክቷል።   

   

በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የወጪ ምርቶች ተወዳዳሪነት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዘሪሁን አበበ ብሪካው ሥራ በመጀመረ ሁለት ወራት ውስጥ ከ400 ሺህ ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ተናግረዋል።       

የቆዳ ተረፈ ምርት ከዚህ በፊት የአከባቢ ብክለትና መጥፎ ሽታ ምንጭ የሚል እይታ በህብረተሰቡ ዘንድ መኖሩን አስታውሰው ፋብሪካው የቆዳ ተረፈ ምርትን በግብዓትነት የሚጠቀም መሆኑ ይሄንን ችግር የሚያቃልል ነው ብለዋል።     

ፋብሪካው ተረፈ ምርቱን ወደ "ጀላቲን" ምርት የሚቀይርበት ሂደት ትልቅ የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚፈጥር ነው።       

ፋብሪካው ስራ ከመጀመሩ በፊት የአዋጭነት ግምገማ መደረጉን የገለጹት ሥራ አስፈጻሚው ፋብሪካው ወደ ሥራ እንዲገባ የሚያስፈልጉ መሳሪያዎች ያለምንም ችግር ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ድጋፍ እንደተደረገም አስረድተዋል።           

ኢንዱስትሪዎች አምርተው ወደ ውጭ የመላክ ሂደቱ ውጤታማ እንዲሆን ሚኒስቴሩ ከጉምሩክ፣ ሎጂስቲክስ፣ ብሄራዊ ባንክን ጨምሮ ከሚለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።   

የፋብሪካው ሥራ አስኪያጅና ባለቤት ጂያንሲንግ ጃንግጃንግ በበኩላቸው ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት ከአምስት የቆዳ ፋብሪካዎች ተረፈ ምርት እየተቀበለ "ጀላቲን" የተሰኘውን ምርት እያመረተ መሆኑን ተናግረዋል።     

በአሁኑ ወቅት ፋብሪካው እንደ መጀመሪያ በአንድ ሳምንት አንድ ኮንቴይነር ምርት እያመረተ መሆኑን ጠቅሰው ወደ ፊት አቅሙን በማሳደግ በወር እስከ 10 ኮንቴይነር ጀላቲን ለማምረት እቅድ ተይዟል ብለዋል።   

እስካሁን በፋብሪካው የተመረተው አስር ኮንቴይነር ምርት ወደ ውጭ ተልኳል፤ ቀሪ አምስት ኮንቴይነሮች ወደ ውጭ ለመላክ ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።     

ፋብሪካውን ምርት ለማከናወን 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተደረገበት መሳሪያ ስራ መጀመሩንም ይፋ አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም