የኢንተርፕራይዞችን የፋይናንስ ፋላጎት ለማሳደግ የሚያስችል "ኢኖቫቲቭ ፋይናንስ ላቭ" የተባለ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
የኢንተርፕራይዞችን የፋይናንስ ፋላጎት ለማሳደግ የሚያስችል "ኢኖቫቲቭ ፋይናንስ ላቭ" የተባለ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ
ጥቅምት 08 ቀን 2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን የፋይናንስ ፋላጎት ለማሳደግ የሚያስችል "ኢኖቫቲቭ ፋይናንስ ላቭ" የተባለ ፕሮጀክት ይፋ አደረጉ።
በዚሁ መርሃ ግብር ከሥራና ክህሎት፣ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ እና ከገንዘብ ሚኒስቴር እንዲሁም ከሌሎች የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ተቋማትን የወከሉ ሰዎች ተገኝተዋል።
ፕሮጀክቱም 2 ሚሊየን የሚሆኑ ጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን የአቅም ግንባታ ስልጠና ለመስጠት፣ የገንዘብ አቅማቸውን ለማሳደግ እና የህግና ፖሊሲ ጥናት በማካሄድ የሚገጥሙ ማነቆዎችን መፍታት የሚያስችል እንደሆነ ተነግሯል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ ሰለሞን ደስታ፤ የገንዘብ ሚኒስቴርና ብሔራዊ ባንክ የካፒታል ማርኬቱን ለማሳደግ ከመንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ጋር በትብብር እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
‘የኢኖቫቲብ ፋይናንሻል ላቭ' ፕሮጀክት አፈፃጸም ለመከታተልም ከመንግስትና የግል ተቋማት፣ ከቴኖሎኖሎጂ ኩባንያዎች እና ሌሎች ግለሰቦች የተውጣጣ አማካሪ ቦርድ እንዳሉት ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱም የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች የሚያመጧቸውን አዳዲስ አሰራሮች ተግባራዊ በማድረግ የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን የፋይናንስ ፋላጎት ለማሳደግ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም የኢትዮጵያ አስተባባሪ ቱራን ሳላኅ፤ የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን በመደገፍ በኢትዮጵያ ብዙ መስራት እንደሚቻል ተናግረዋል።
‘የኢኖቫቲቭ ፋይናንሻል ላቭ' ፕሮጀክትም የኢንተርፕራይዞችን የገንዘብና ቴክኖሎጂ አቅርቦት፣ የንግድ ስራና ፋይናንስ ተደራሽነትን ለማሳደግ መልካም እድል ይዞ መምጣቱን ገልጸዋል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም የአካታች ኢኮኖሚያዊ ልማት ንዑስ አስተባባሪ ግዛቸው ሲሳይ፤ ኢኖቫቲቭ ፋይናንሻል ላቭ ኢንተርፕራይዞች የሚገጥሟቸውን የገንዘብ ክፍተቶች ለመሙላት ሁነኛ መፍትሄ ይዞ መምጣቱን ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱም አዳዲስ የብድር አቅርቦቶችን በጥናት በማስደገፍ የኢንተርፕራይዞችን የገንዘብ አቅም ለማሳደግ የጎላ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
ኢኖቫቲቭ ፋይናንስ ላቭ ፕሮጀክት ከብሔራዊ ባንክ፣ ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ከገንዘብ ሚኒስቴርና እንዲሁም ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም የተውጣጡ 17 የቦርድ አባላት እንዳሉት ተገልጿል።