ቅዱስ ጊዮርጊስ በማሸነፍ ጉዞው ሲቀጥል ሐዋሳ ከተማ በሊጉ 2ኛ ድሉን አስመዝግቧል - ኢዜአ አማርኛ
ቅዱስ ጊዮርጊስ በማሸነፍ ጉዞው ሲቀጥል ሐዋሳ ከተማ በሊጉ 2ኛ ድሉን አስመዝግቧል
ጥቅምት 8 2015 (ኢዜአ) በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቅዱስ ጊዮርጊስ በማሸነፍ ጉዞው ሲቀጥል ሐዋሳ ከተማ ሁለተኛ ድሉን አስመዝግቧል።
የፕሪሚየር ሊጉ 4ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች ዛሬ በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ተደርገዋል።
የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ የቶጎው የፊት መስመር ተጫዋች ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ በጨዋታና በፍጹም ቅጣት ምት ባስቆጠራቸው ግቦች አዳማ ከተማን 2 ለ 1 ተሸንፏል።
አጥቂው በሊጉ ያስቆጠራቸውን ግቦች ወደ ስምንት ከፍ በማድረግ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን እየመራ ነው።
ዳዋ ሁቴሳ ለአዳማ ከተማ ብቸኛዋን ግብ ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ውጤቱን ተከትሎ ፈረሰኞቹ በፕሪሚየር ሊጉ ያደረጋቸውን አራት ጨዋታዎች በማሸነፍ በ12 ነጥብ መሪነታቸውን አጠናክረዋል።
በሊጉ ሁለተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው አዳማ ከተማ በስድስት ነጥብ በነበረበት ሶስተኛ ደረጃ ላይ ነው።
ሰባት ግቦች በተቆጠሩበት ሌላኛው የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታ ሐዋሳ ከተማ ወልቂጤ ከተማን 4 ለ 3 አሸንፏል።
በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ከፋሲል ከነማ ሐዋሳን የተቀላቀለው ሙጂብ ቃሲም ሶስት ግቦችን በማስቆጠር ሀትሪክ ሲሰራ ኤፍሬም አሻሞ ቀሪዋን ግብ አስቆጥሯል።
ለወልቂጤ ከተማ የቡድኑ አምበል ጌታነህ ከበደ በጨዋታና በፍጹም ቅጣት ምት ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ብዙአየሁ ሰይፈ ቀሪዋን ግብ ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ውጤቱን ተከትሎ ሐዋሳ ከተማ በስድስት ነጥብ ከነበረበት 11ኛ ደረጃ ወደ 4ኛ ከፍ ሲል ወልቂጤ ከተማ ደግሞ በተመሳሳይ ስድስት ነጥብ ብዙ ጎል ባገባ በሚለው ህግ ከ4ኛ ወደ 5ኛ ደረጃ ዝቅ ብሏል።
ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የአራተኛ ሳምንት መርሐግብር ነገም ሲቀጥል አርባምንጭ ከተማ ከሀድያ ሆሳዕና ከቀኑ 7 ሰአት እንዲሁም ባህር ዳር ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ ከቀኑ 10 ሰአት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።