ለአየር መንገዱ የስኬት ጉዞ የቦይንግ 787 አውሮፕላኖች የላቀ ሚና አላቸው-- የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ - ኢዜአ አማርኛ
ለአየር መንገዱ የስኬት ጉዞ የቦይንግ 787 አውሮፕላኖች የላቀ ሚና አላቸው-- የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ
ጥቅምት 08 /2015 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ አየር መንገድ የስኬት ጉዞ ውስጥ የቦይንግ 787 አውሮፕላኖች የላቀ ሚና እንዳላቸው የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።
አየር መንገዱ የቦይንግ 787 አውሮፕላኖችን ወደ አገር ውስጥ በማስመጣት አገልግሎት መስጠት የጀመረበትን 10ኛ ዓመት የቦይንግ ኩባንያ ምክትል ስራ አስፈጻሚና ከፍተኛ ሃላፊዎች በተገኙበት አክብሯል።
አየር መንገዱ በወቅቱ ቴክኖሎጂ ከረቀቁና ለመንገደኞች ምቹ ከሆኑ አውሮፕላኖቹ አንዱ የሆነውን ቦይንግ 787 አውሮፕላን ከዛሬ 10 ዓመት በፊት በማስመጣት በአፍሪካ ቀዳሚ ነበር።
የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በአየር መንገዱ የስኬት ጉዞ የቦይንግ አውሮፕላኖች አገልግሎት መስጠት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ የላቀ ሚና መወጣታቸውን ገልጸዋል።
ዛሬ ላይ 27 የቦይንግ 787 ድሪምላይነር የመንገደኛ አውሮፕላኖች እንዳሉት ገልጸው አውሮፕላኖቹ በዘርፉ የረቀቀ የተባለው ቴክኖሎጂ የተገጠመላቸው መሆናችውን ተናግረዋል።
በቀጣይ አየር መንገዱ ስኬቱን በማስቀጠል ወደ ላቀ ደረጃ ለመድረስ ተጨማሪ የቦይንግ 787 አውሮፕላኖችን በማስመጣት ወደ አገልግሎት እንዲገቡ ያደረጋል ብለዋል።
የቦይንግ ኩባንያ ምክትል ፕሬዚደንት ማይክ ሲኔት፤ በአፍሪካ በስኬቱ መሪ ከሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመስራታችን በእጅጉ ደስተኞች ነን ነው ያሉት።
በቀጣይም አየር መንገዱ ወደ ላቀ ደረጃ ለመጓዝ በሚያደርገው ጥረት የቦይንግ ኩባንያ አብሮ የሚዘልቅ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኞች በትብብር የመስራት ልምዳቸው አስደናቂ መሆኑን ገልጸው ይህም በላቀ መልኩ በሁለንተናዊ ቁመናው እንዲቀጥል እንደሚያደርገው አምናለሁ ብለዋል።