ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን የልማትና የብልጽግና ጉዞ ለማደናቀፍ የሚጥሩ አካላትን መመከት የጋራ ሃላፊነታችን ሊሆን ይገባል- ዶክተር ዓለሙ ስሜ

ጥቅምት 08/2015(ኢዜአ) ለውጭ ኃይሎች በመላላክ የኢትዮጵያን የልማትና የብልጽግና ጉዞ ለማደናቀፍ የሚጥሩ አካላትን መመከት የሁላችንም የጋራ ሃላፊነት ሊሆን ይገባል ሲሉ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ማስተባበሪያ ማዕከል አስተባባሪ ዶክተር ዓለሙ ስሜ ተናገሩ፡፡

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጎብኝተዋል፡፡

ጉብኝቱን የመሩት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ማስተባበሪያ ማዕከል አስተባባሪ ዶክተር ዓለሙ ስሜ፤ የሕዳሴ ግድብ የሁሉም አሻራ ያረፈበት የኢትዮጵያዊያን አንጡራ ሃብት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ግድቡን መጎብኘታቸው በኢትዮጵያ ጥቅም ላይ በጋራ ለመቆማቸው ዋነኛ ማሳያ መሆኑን ያሳዩበት ነውም ብለዋል።

"ኢትዮጵያዊያን የፖለቲካ ልዩነት ሳይገድበን ለአገር ጥቅም በጋራ መቆም አለብን" ያሉት ዶክተር ዓለሙ፤ ለውጭ ኃይሎች በመላላክ የኢትዮጵያን የልማትና ብልጽግና ጉዞ ለማደናቀፍ የሚጥሩ አካላትን መመከት የሁላችንም የጋራ ሃላፊነት ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።

ለፖለቲካ የሃሳብ የበላይነት እየተፎካከርን አገርን በሚጠቅሙ ብሄራዊ ጉዳዮች ላይ ደግሞ በጋራ መሥራት ይኖርብናል ሲሉ ተናግረዋል።

"ኢትዮጵያ ለሁላችንም የሚበቃና ለሌሎችም የሚተርፍ ሃብት ያላት አገር ነች" ያሉት ዶክተር ዓለሙ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ለሚሰሩ የውጭ ጠላቶች የሚላላኩ የፖለቲካ ሃይሎች ከእኩይ ዓላማቸው ሊታቀቡ ይገባል ብለዋል።

የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመጭው ትውልድ ለማስተላለፍ በሚደረገው ጥረት ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

በተሳሳተ አመለካከት ጠመንጃ ይዘው ኢትዮጵያን በመውጋት ላይ የሚገኙ አካላትም ቆም ብለው በማሰብ ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጉብኝት ከ50 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተውጣጡ አመራሮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም