ቀጥታ፡

የሰንደቅ አላማ ቀን ሲከበር ለአገር ክብር፣ ሰላምና ደህንነት የተገባውን ቃል ኪዳን በብቃት ለመፈፀም በመዘጋጀት ነው- ምክትል ኮሚሸነር መንገሻ ሞላ

ጥቅምት 07 ቀን 2015 (ኢዜአ) የሰንደቅ አላማ ቀን ሲከበር ለአገር ክብር፣ ለህዝብ ሰላምና ደህንነት የተገባውን ቃል ኪዳን በብቃት ለመፈፀም በመዘጋጀት መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ የወንጀልና የትራፊክ አደጋ ዘርፍ ምክትል ኮሚሸነር መንገሻ ሞላ ገለጹ።

15ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን "ሰንደቅ ዓላማችን የብዝሃነታችን መገለጫ፤ የሉዓላዊነታችን ምሰሶ" በሚል መሪ ሃሳብ በብሔራዊ ደረጃ ተከብሮ ውሏል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሰንደቅ ዓላማ ቀንን ሠራተኞቹና አመራሮቹ በተገኙበት በቅጥር ግቢው በተለያዩ ዝግጅቶች አክብሯል።

በአከባበር ስነ-ስርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ምክትል ኮሚሸነር መንገሻ ሞላ፤ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የአፍሪካ የነፃነት ተምሳሌትና የብሔራዊ አንድነት መገለጫ በመሆኑ ትልቅ ክብር ሊሰጠው እንደሚገባ ገልጸዋል።

የመስዋዕትነት፣ የሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነትና የአብሮነት መገለጫ መሆኑን የገለጹት ምክትል ኮሚሸነሩ፤ በተለይም ለፖሊስ አርማውና መለያው በመሆኑ ልዩ ትርጉም አለው ብለዋል።

በመሆኑም ፖሊስ የሰንደቅ ዓላማን ቀን ሲያከብር ለአገር ክበር፣ ለህዝብ ሰላምና ደህንነት የገባውን ቃል ኪዳን በብቃት ለመፈፀም በመዘጋጀት መሆኑንም ተናግረዋል።

የሕዝቦችን ሰላምና ደኅንነት ከማስጠበቅ አንፃር የተሰጠውን ተልዕኮ ከመቼውም ጊዜ በላይ ለማሳካት ዳግም ቃል በመግባት መሆኑንም ገልጸዋል።

በአከባበር ስነ-ስርዓቱ ላይ ያነጋገርናቸው የፖሊስ አባላትም ሰንደቅ ዓላማ የሀገር አንድነትና የነፃነት አርማ በመሆኑ ተገቢው ክብር እንዲሰጠው እንሰራለን ብለዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያውያን ለሰላምና አብሮነታቸው ለሰንደቃቸው ክብር ሲሉ በጋራ ሊቆሙ ይገባል ብለዋል።

ፖሊስ ለሕግ የበላይነት መከበር የሚያደርገውን ጥረት የህዝቡ ትብብርና ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም