የሰንደቅ ዓላማ ታሪክና ለአገር ክብር ሲባል የተከፈለለትን መስዋዕትነት ትውልዱ በአግባቡ እንዲገነዘበው ማድረግ ይገባል- ልጅ ዳንኤል ጆቴ

19

ጥቅምት 07 ቀን 2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ታሪክና ለአገር ክብር ሲባል የተከፈለለትን መስዋዕትነት የአሁኑ ትውልድ በቅጡ እንዲገነዘበው ማድረግ እንደሚገባ የጥንታዊት ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዝዳንት ገለጹ።

የጥንታዊት ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ፤ የቀደሙት አያቶች በከፈሉት መስዋዕትነት የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የሰንደቋ ክብር ተጠብቆ መቀጠሉን ይናገራሉ።

የተከፈለው መስዋዕትነት የቅኝ ግዛት ቀንበርን በማስወገድ ለጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ትግል መሰረት የጣለ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ነፃነቷ ያልተደፈረ የራሷ ባህል፣ ቋንቋና ታሪክ ያላት ታላቅ አገር መሆኗንም ለዓለም ሕዝብ ያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ ሁሉ ሂደት የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የጀግንነት መገለጫና የነፃነት ተምሳሌት ተደርጎ እስካሁንም መዝለቁን ገልጸዋል።

በመሆኑም የአሁኑ ትውልድ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ታሪክና ለአገር ክብር ሲባል የተከፈለለትን መስዋዕትነት በአግባቡ እንዲገነዘበው ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

አባት አርበኛ መቶ አለቃ አብዲሳ ብሩ፤ የኢትዮጵያ ምሰሶ የሆነውን አንድነት በማጠናከር ለአገር እድገት መሥራት ይገባል በማለት ተናግረዋል።

የሰንደቅ ዓላማ ቀን በየዓመቱ መከበሩ ትውልዱ ለሰንደቅ ዓላማ ያለውን ትርጉምና የተከፈለውን መስዋዕትነት በአግባቡ እንዲገነዘብ አስተዋጽኦ እንዳለው ጀግኖች አባቶች ገልጸዋል።

የሰንደቅ ዓላማ ቀን "ሰንደቅ ዓላማችን የብዝሃነታችን መገለጫ፤ የሉዓላዊነታችን ምሰሶ" በሚል መሪ ሃሳብ በብሔራዊ ደረጃ  ለ15ኛ  ጊዜ ተከብሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም