ቀጥታ፡

የመጀመሪያው ሩብ ዓመት አፈጻጸም በሁሉም ሴክተሮች ጥሩ ክንውንና ውጤት የተመዘገበበት ነው- ሚኒስትሮች

ጥቅምት 7/2015 (ኢዜአ) የበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም በሁሉም ሴክተሮች ጥሩ ክንውንና ውጤት የተመዘገበበት መሆኑን ሚኒስትሮች ገለጹ።

የ2015 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚና የዘርፎች አፈጻጸም ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት በጎንደር ከተማ ተከናውኗል።

አጠቃላይ በየሴክተር መሥሪያ ቤቶች የሩብ ዓመቱ ክንውን በብዙ መልኩ ጥሩ ውጤት የተመዘገበበት መሆኑን ሚኒስትሮች ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በቱሪዝም ዘርፍ በተለይም በአገር ውስጥና በውጭ የማስተዋወቅ ሥራ በስፋት ተከናውኗል።

የአገር ውስጥ የቱሪዝም ንቅናቄ ጥሩ ስኬት የተገኘበት ሲሆን በውጭ አገርም በተለይም ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር የተሰሩ ሥራዎችን በሚመለከት የቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ አብራርተዋል።

የኮንፈረንስ ቱሪዝም በሦስት ወራት ጥሩ አፈጻጸም የታየበት መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይ በተለይም አገር አቀፍ የቱሪዝም ሃብት ልየታ፣ የቱሪዝም ልማት ፕሮግራም መቅረጽና የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት እውን ማድረግ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።

በባህልና ስፖርት ዘርፍም የስፖርት ማዘውተሪያና የስታዲየም ግንባታ ሂደት ጥሩ አፈጻጸም ላይ መሆኑን ሚኒስትሩ ቀጄላ መርዳሳ ተናግረዋል።

የስፖርት ዘርፉን ውጤታማነት ማጠናከር፣ የባህል ትስስርና የፈጠራ ዘርፍ እንዲሁም የቋንቋ ፖሊሲ ትግበራን በተመለከተ ከአሥር ዓመቱ መሪ እቅድ ጋር በማስተሳሰር የተጀመሩ ሥራዎች አበረታች መሆናቸው ተመልክቷል።

የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዷለም በበኩላቸው፤ ከለውጡ ጋር ተያይዞ በተለይም የሰላም እጦት ችግሮችን ለመፍታት በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በጦርነትና ግጭት ምክንያት በርካታ ዜጎች ለመፈናቀልና ሞት ሲዳረጉ የንብረት ውድመትና ተያያዥ ችግሮች እንደነበሩ አስታውሰው፤ በዘላቂነት ሰላምን የመገንባት የተለያዩ ጥረቶች መደረጋቸውን ጠቅሰዋል።

የሚያጋጥሙ ችግሮች በጦርነት መፈታት እንደማይችሉ የመንግሥት ጽኑ እምነት ስላለ ለሰላም አማራጮች ልዩ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም በብዙ መልኩ የሰላም ግንባታ ሥራን ለማጠናከር የውይይትና የንግግር መድረኮች የመፍጠር እንዲሁም የአንድነትና አብሮነት እሴቶች እንዲጎለብቱ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

በሩብ ዓመቱ አፈጻጸም የኢኖቬሽንና ምርምር ዘርፍ የተሳካ ውጤት የታየበት ሲሆን የመንግሥት አሰራሮችን ቀልጣፋ ለማድረግ የኤሌክትሮኒክስ አሰራር ሥርዓት በስፋት መተግበሩን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር በለጠ ሞላ ገልጸዋል።

በምርምር ዘርፍ ሥራ ፈጣሪዎችን ማበረታታትና የሙያ ክህሎት ማዕከል ግንባታን ማሳካት ተችሏልም ነው ያሉት።

በ2015 የሚቋጩ በጅምር ላይ ያሉ በርካታ ሥራዎች እንዳሉ ጠቅሰው፤ ለስኬቱ የክትትልና ቁጥጥር ሥራው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ተናግረዋል።

የከተማ ግብርናን ከአረንጓዴ ልማት በማስተሳሰር እንዲሁም ከተሞችን በማስዋብና አረንጓዴ አሻራን ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ አበረታች ተግባራት ማከናወኑን የከተማና መሰረተ-ልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ ተናግረዋል፡፡

አዳዲስ የመንገድ ግንባታ 88 በመቶ እንዲሁም የተበላሹ መንገዶች ጥገና የተሻለ አፈጻጸም መመዝገቡን ጠቅሰው፤ የኮንስትራክሽን ዘርፉን በአዳዲስ ቴክኖሎጂ የመደገፍ ሥራም ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።

የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጂነር ታከለ ኡማ፤ የማዕድን ዘርፉን የወጪ ንግድ ለማሳደግ እየተሰሩ የሚገኙ ሥራዎች ለውጥ ማስገኘታቸውን ጠቁመዋል፡፡

በኩባንያ ደረጃ የሚመረተው የወርቅ ምርት ጭማሪ ማሳየቱን በመጠቆም በባህላዊ ደረጃ የሚመረተው ወርቅ ግን በኮንትሮባንድና በሕገ-ወጥ አሰራር ምክንያት በተፈለገው ልክ አለመሆኑን አንስተዋል፡፡

የፀጥታ ችግርና ኮንትሮባንድ ዘርፉ ተግዳሮቶች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በቀጣይ ችግሩን ለመፍታት ከክልሎችና ባለድርሻ አካላት ጋር ይሰራል ብለዋል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ባለፉት ሦስት ወራት በተለየ ሁኔታ የለውጥ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱንና በክህሎት ልማትና በሥራ ዕድል ፈጠራ አበረታች ተግባር ማስመዝገቡም ተገልጿል፡፡

የውጭ ምንዛሬ ሊያስገኙ የሚችሉ ዲጂታል ኢንተርፕራይዞችን በማስፋፋት የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት ለውጥ እያሳዩ መሆናቸውንም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ገልጸዋል።፡

ሚኒስቴሩ የአሰሪና ሠራተኛ ግንኙነቱን በማሳለጥ የኢንዱስትሪ ሰላም ለማስፈንና የፐብሊክ ኢንተርፕርነርሺፕን በማጠናከር መንግሥታዊ ተቋማት ችግር ፈቺ እንዲሆኑ የሚያግዙ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ክንውን በዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚ አመላካቾች ጥሩ ውጤት የተመዘገበበት ሲሆን አጠቃላይ አገራዊ የኢኮኖሚ እድገቱም 6 ነጥብ 4 በመቶ መሆኑ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም