ቀጥታ፡

የአንድነታችን መገለጫ የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ ስናከብር ለአገራችን ክብርና ሉዓላዊነት በጋራ በመቆም ነው

ጥቅምት 07 ቀን 2015 (ኢዜአ) የክብራችንና የአንድነታችን መገለጫ የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ ስናከብር ለአገራችን ክብርና ሉዓላዊነት መከበር በጋራ በመቆም ነው ሲሉ የኢዜአ አመራርና ሰራተኞች ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት /ኢዜአ/ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች 15ኛውን የሰንደቅ ዓላማ ቀን አክብረዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የኢዜአ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ፤ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የግዛት አንድነትና የሕዝቦችን አብሮነት በማጽናት ሂደት የገዘፈ ታሪክ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው ክብርና ሉዓላዊነት ሲሉ አሁንም በጀግንነት መስዋእትነት እየከፈሉ መሆኑን ተናግረዋል።

የክብራችንና የአንድነታችን መገለጫ የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ ስናከብር ለአገራችን ክብርና ሉዓላዊነት መከበር በትብብርና በጋራ በመቆም ነው ብለዋል።

የሰንደቅ ዓላማ ቀን ሲከበር አብሮነትን በማጽናትና አንድነትን በማጠናከር እንዲሁም የኢትዮጵያ ክብርና ሉዓላዊነት በጋራ ለማስጠበቅ ይበልጥ በመዘጋጀት ጭምር መሆን አለበት ሲሉም ገልጸዋል።

የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ቀኑን ሲያከብሩ የሰንደቅ ዓላማን ትርጉም በአግባቡ በመረዳት አብሮነትን የሚያጠናክሩ ተግባራትን በማከናወን መሆኑን እንዳለበት ጠቅሰው ከዚህ አንጻር ከመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ብዙ ስራ ይጠበቃል ነው ያሉት።

እለቱን በማክበር ላይ የነበሩ የተቋሙ ሠራተኞችም የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የአፍሪካ የነፃነት ተምሳሌትና የአሸናፊነት ምልክት በመሆኑ በሚገባው ክብር ልክ ልናከብረው ይገባል ብለዋል።

የዘንድሮው የሰንደቅ አላማ ቀን ”ሰንደቅ ዓላማችን የብዝሃነታችን መገለጫ፤ የሉዓላዊነታችን ምሰሶ ነው!" በሚል መሪ ሃሳብ ተከብሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም