ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት መገለጫ የሆነው ሰንደቅ ዓላማ የበርካታ አፍሪካ አገራት ምልክት መነሻ በመሆኑ ኩራት ይሰማናል - ወይዘሮ ዓለምፀሐይ ጳውሎስ

ጥቅምት 07 ቀን 2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት መገለጫ የሆነው ሰንደቅ ዓላማ የበርካታ አፍሪካ አገራት ምልክት መነሻ በመሆኑ ኩራት ይሰማናል ሲሉ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የአገልግሎቶችና የመልካም አስተዳደር ክትትል ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዓለምፀሐይ ጳውሎስ ገለጹ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አመራርና ሠራተኞች 15ኛውን የሰንደቅ ዓላማ ቀን በጽሕፈት ቤቱ ቅጥር ግቢ በድምቀት አክብረውታል።

ዕለቱን አስመልክቶም የጽሕፈት ቤቱ የአገልግሎትና መልካም አስተዳደር ክትትል ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ  ዓለምፀሐይ ጳውሎስ፤ ሰንደቅ ዓላማችን የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት መገለጫ ነው ብለዋል።

የሰንደቅ ዓላማ ቀን ዕለት ሲታሰብም የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ምሰሶና የአንድነት መገለጫ መሆኑን በቅጡ መገንዘብ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የሰንደቅ ዓላማ መታሰቢያ ቀንም በአንድ ቀን ብቻ ታስቦ የሚያልፍ ሳይሆን ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ የምትወከልበት ምልክት ሆኖ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ለበርካታ የአፍሪካ አገራት መነሻ ዓርማና ምልክት በመሆኑም ትልቅ ኩራትና ክብር ይሰማናል ብለዋል።

ኢትዮጵያዊያንም የአገራቸው ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ በየተሰማሩበት የሥራ መስክ  ውጤታማ ሥራን ማከናወን እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የአገርን ሉዓላዊ አንድነት አስከብሮ ማስቀጠል የሚቻለው በሁሉም መስክ በሚደረግ ድምር ውጤት መሆኑን ጠቅሰው፤ በልማትና አገልግሎት ዘርፍም ውጤታማ ሥራ ማከናወን ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ሰላሟን በማረጋገጥ ልማቷን አስቀጥላ የሰነቀችው የብልጽግና ጉዞ እውን እንዲሆን ኢትዮጵያዊያን በተሻለ ተነሳሽነት አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ የሚንፀባረቁ ሕብረ-ብሔራዊ ብዝሃነትን እንደ ውበት በመጠቀም የትስስር መገለጫ አድርጎ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።

አንድነት ለአገር እድገትና ብልጽግና ሁነኛ መሳሪያ በመሆኑ ኢትዮጵያዊያንን ለመከፋፈል ለሚጥሩ አካላት እድል ባለመስጠት ሰንደቅ ዓላማን የትስስር ገመድ አድርጎ መጠቀም ያስፈልጋልም ብለዋል።

15ኛው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ቀን "ሰንደቅ ዓላማችን የብዝሃነታችን መገለጫ፤ የሉዓላዊነታችን ምሰሶ" በሚል መሪ ሃሳብ በመላ አገሪቱ በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም