ቀጥታ፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ እውቅና ለሰላምና ለይቅርታ ይበልጥ እንድንሰራ አነቃቅቶናል---የጋሞ የሃገር ሽማግሌዎች

አርባምጭ መስከረም 13/2011 በአርባምንጩ ተቃውሞ ግጭት እንዳይሰፋ ለተጠቀምንበት ባህላዊ ክዋኔ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጠው እውቅና ለሠላም ይበልጥ እንድንሠራ የሚያበረታታ ነው" ሲሉ የጋሞ ባይራ ሽማግሌዎች ገለጹ። ባይራዎቹ በቡራዩ ጥቃት ዙሪያ ከአባ ገዳዎች ጋር ቀርቦ ለመወያየትና በጋራ መፍትሔ ለማስቀመጥ  ፍላጎት እንዳላቸው ለኢዜአ ተናግረዋል። ከባይራዎቹ መካከል አቶ ሰድቃ ስሜ በሰጡት አስተያየት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ለጋሞ እርቀሠላም ባህልና ባይራዎቹ የሰጡት እውቅና አስደስቷቸዋል። በብሔረሰቡ ባህል እርጥብ ሳር የያዘ ታላቅ እንደማይነካና እጅግ እንደሚከበር ገልጸው፤ ሽማግሌዎችን በማክበርና ለስርዓቱ ተገዥ በመሆን ከድርጊቱ የተቆጠቡ ወጣቶችንም አመስግነዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ለዚህ ተግባር የሰጡት እውቅና ለሠላም ይበልጥ ተግተው እንዲሠሩ እንዳበረታታቸውም ተናግረዋል። ሌላው ባይራ አቶ አንጁሎ አርሼ በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ለባህሉ ለሰጡት እውቅና አመስግነዋል። የጋሞ የእርቅና የሠላም እሴቶች ከእሳቸው ይቅርታ፣ ፍቅርና መደመር ፍልስፍናዎች ጋር እጅጉን እንደሚመሳሰሉም ገልጸዋል። በቡራዩ ግጭት የጋራ ምክክር ላማድረግ በባህሉ መሠረት ከኦሮሞ አባገዳወች ጥሪ እየጠበቁ መሆናቸውን ገልጸው፤ ጥያቄው ሲቀርብ ለመገናኘት ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል። በጋሞ ባህል "እርጥብ ሳርን የሚያሸንፍ ጦር የለም" ያሉት አቶ አንጁሎ "ስርዓቱ የአርባምንጭ ወጣቶችን ቁጣ በማቀዝቀዝ ያስገኘው ውጤት ለሌሎችም አስተማሪ ነው" ብለዋል። አቶ አመሌ አልቶ የተባሉ ሽማግሌም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እውቅና አመስግነው፤ በቡራዩ ግጭት እጅግ ማዘናቸውን ተናግረዋል፡፡ የጋሞ ጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኢሳያስ እንድሪያስ በበኩላቸው የጋሞ አባቶች ጠብቀው ያቆዩትን የእርቅ ባህል ወጣቱ ትውልድ ለሰለጠነው ዓለም በማስተዋወቅ ለዳበረ ዲሞክራሲ እንዲጠቀሙበት ጠይቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለባህሉና ባይራዎች ለሰጡት እውቅና አመስግነው ባህሉ ይበልጥ እንዲዳብር የዞኑ አስተዳደር ከወጣቶችና ምሁራን ጋር በመሆን እንደሚሠራም ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፖርቲ (ኦዴፖ) ድርጅታዊ ጉባኤ ማጠቃሊያ የጋሞ የሀገር ሽማግሌዎች የአርባምንጩን ግጭት ለመከላከል ለተጠቀሙት ባህላዊ ስርዓት እውቅና መስጠታቸው ይታወሳል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም