የሰንደቅ ዓላማ ቀን በክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ተከበረ - ኢዜአ አማርኛ
የሰንደቅ ዓላማ ቀን በክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ተከበረ
ጥቅምት 7/2015 (ኢዜአ) የሰንደቅ ዓላማ ቀን “ሰንደቅ ዓላማችን የብዝኃነታችን መገለጫ፤ የሉዓላዊነታችን ምሰሶ ነው” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በድምቀት ተከብሯል።
በአዲስ አባባ በተካሄደው መርሃ-ግብር ላይ የከተማዋ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ቡዜና አልቃድር እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የስራ ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ እና ሌሎች የምክር ቤቱና የከተማ አስተዳደሩ አመራሮችና ሰራተኞች ተገኝተዋል።
ምክትል ከንቲባው ባደረጉት ንግግር “ዜጎች ለሀገራቸው ያላቸውን ፍቅርና ብሔራዊ ስሜት ለሰንደቅ ዓላማ በሚሰጡት ክብር ይገለጻል ብለዋል፡፡
በአማራ ክልል ባህርዳር ከተማ በተካሄደው የአከባበር ስነ-ስርዓት ላይ የክልሉ አፈ-ጉባኤን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች ተሳትፈዋል።
ቀኑ በኦሮሚያ ክልል ደረጃ የተከበረ ሲሆን በፕሮግራሙ ላይ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ኢደኤ ባደረጉት ንግግር "ሰንደቅ አላማ የአንድ ሀገር የነፃነትና የማንነት መገለጫ በመሆኑ ለሰንደቅ አላማችን ክብር ልንሰጥ ይገባል ፤ይህም አስፈላጊ ነው" ብለዋል።
በሲዳማ ክልል በሀዋሳ ከተማ በተከበረው የሰንደቅ አላማ ቀን ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳደር ደስታ ሌዳሞ "ሰንደቅ ዓላማችን የሀገራችን ክብርና የሉአላዊነት መገለጫ በመሆኑ ለሰንደቅ ዓላማ ክብር የደም ዋጋ ለከፈሉ ሁሉ ክብር ይገባቸዋል" ሲሉ ተናግረዋል።
በሶማሌ ክልል ደረጃ በጅግጂጋ ከተማ በተከበረው ስነ-ስርዓት ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሁመድን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ነው የተከበረው።
በዓሉ በክልሉ ከተሞችም በድምቀት መከበሩ ተመላክቷል።
በተመሳሳይ ቀኑ በአፋር ክልል የተከበረ ሲሆን የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አወል አርባና የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ በክልሉ ቤተ-መንግስት የሰንደቅ ዓላማ በመስቀልና ቃለ-መሃላ በመፈጸም ስነ-ስርዓት ተከብሯል።
በጋምቤላ ክልል በተከናወነው የሰንደቅ ዓላማ አከባበር ስነ-ስርዓት ለይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ ባደረጉት ንግግር ሰንደቅ ዓላማ የኢትዮጵያ ህዝቦች የህብረ ብሄራዊ አንድነትና የሉዓላዊነት መገለጫ አርማ ነው ብለዋል።
በተመሳሳይ በደቡብ ምዕራብ ህዝቦች ክልል የሰንደቅ ዓላማ ቀን በክልሉ ቦንጋ ከተማ ለመጀመሪያ ግዜ የተከበረ ሲሆን በዓሉን አስመልክቶ የፓናል ውይይት ተከናውኗል።
በድሬደዋ ከተማ በተካሄደው አከባበር ላይ የአስተዳደሩ ከንቲባ ከድር ጁሀር እና ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች በተሳተፉበት የተከበረ ሲሆን ሰንደቅ አላማ የመስቀል ስነ-ስርዓት በማከናወን ተከብሯል።
15ኛው ብሄራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በሀረሪ ክልል እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማም በድምቀት ተከብሮ ውሏል።