ቀጥታ፡

የሉአላዊነት መገለጫ ለሆነው ሰንደቅ አላማ ዋጋ በመክፈል ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማድረስ መከላከያ ሠራዊቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ ነው- ሌተናል ጀነራል ይመር መኮንን

ጥቅምት 07/2015(ኢዜአ) የአገር ክብርና ሉዓላዊነት መገለጫ ለሆነው ሰንደቅ አላማ ዋጋ በመክፈል ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማድረስ መከላከያ ሠራዊቱ ከመቼውም በላይ ዝግጁ መሆኑን የመከላከያ የትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ ሃላፊ ሌተናል ጀነራል ይመር መኮንን ተናገሩ።

15ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን "ሰንደቅ ዓላማችን የብዝኃነታችን መገለጫ፤ የሉዓላዊነታችን ምሶሶ ነው" በሚል መሪ  ሀሳብ በመከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ መምሪያ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።     

ክብረ በዓሉ የመከላከያ ሚኒስትር ደኤታ ማርታ ሊዊጂ፣ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች፣ የሰራዊቱ አባላትና ሲቪል ሰራተኞች በተገኙበት በደማቅ ስነ ስርአት ተከብሯል።      

የመከላከያ የትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ ሃላፊ ሌተናል ጀነራል ይመር መኮንን በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ በህዝቡና አጠቃላይ በሰራዊቱ ዘንድ ትልቅ ክብር የሚሰጠው ነው ብለዋል።

"ጥንት አባቶቻችን የኢትዮጵያን አንድነት ለማስጠበቅ መስዋዕትነት የከፈሉለት ታሪካዊ ሰንደቅ አላማ ነው" ያሉት ሃላፊው የአሁኑ ትውልድም ለአገሩና ለሰንደቁ ሲል አኩሪ ገድል እየፈጸመ መሆኑን ተናግረዋል።

ሰንደቅ ዓላማ የአገር ክብርና ሉዓላዊነት መገለጫ እንደመሆኑ ጀግኖች ኢትዮጵያዊያን መከፈል ያለበትን ሁሉ መስዋዕትነት ከፍለዋል፤ በቀጣይም ኢትዮጵያ ወደ ተሻለ ምዕራፍ እንድትደርስ ያለንን ሁሉ ለመስጠት ቆርጠን ተነስተናል ነው ብለዋል።       

ኢዜአ ያነጋገራቸው የሰራዊቱ አባላት በበኩላቸው የኢትዮጵያን ከፍታ ለማረጋገጥ በሚሰጠን ግዳጅ ሁሉ ተሰልፈን አገር የሚያኮራ ተግባር ለመፈጸም ዝግጁ ነን ሲሉ ገልጸዋል።  

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ኮለኔል ለገሰ ተሾመ፤ በሚሰጠን ግዳጅ ላይ ሁላችንም እየተሳተፍን ነው፤ የአገርን ቀጣይነት በአስተማማኝ መሰረት ላይ ለማኖር ዝግጁ ነን ሲሉ አረጋግጠዋል።

የሰንደቅ ዓላማ ቀን እየተከበረ ያለው አገር ለማፍረስ ሲጥር የነበረው የአሸባሪው ህወሃት እኩይ ተግባር በተቀለበሰበት አጋጣሚ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል ያሉት ደግሞ ሻምበል ጥላሁን እሸቱ ናቸው።   

የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላምና ብልጽግና እውን ለማድርግ ቃል በገባነው መሰረት የሚጠበቅብንን ሁሉ ለማድረግ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተዘጋጅተናል ብለዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም