ቀጥታ፡

የስታትስቲክስ አገልግሎት የሚያመነጫቸው መረጃዎች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁና የተሟላ ጥራት ያላቸው እንዲሆኑ እየተሰራ ነው

ጥቅምት 07 ቀን 2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት የሚያመነጫቸው መረጃዎች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁና የተሟላ ጥራት ያላቸው እንዲሆኑ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገለጸ።

አገልግሎቱ ከተባበሩት መንግሥታት የኢኮኖሚ ኮሚሽን፣ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስታትስቲክስ ዲቪዠን፣ ከኢትዮጵያ ስታትስቲክስ ባለሙያ ማህበር እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የስታትስቲክስ መረጃ ጥራት በሚጠበቅበት መንገድ ለሚመለከታቸው አካላት ሥልጠናዎችን እየሰጠ ይገኛል፡፡

በሥልጠናው የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት መሥሪያ ቤት አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም የክልል ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤት የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡

የሥልጠናው ዋና ዓላማ መረጃ የሚያመነጩ አካላት መረጃ በሚሰበስቡበት፣ በሚተነትኑበት እና በሚያሰራጩበት ወቅት ጥራት ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ ግንዛቤ ለመስጠት ነው ተብሏል፡፡

የመረጃ ጥራትን ከማስጠበቅ በተጨማሪ የስታትስቲክስ ሥርዓቱ የሚመራበትና ቁጥጥር የሚደረግበትን አግባብ ማስገንዘብም ሌላኛው የሥልጠናው አካል ነው፡፡

የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር  ቢራቱ ይገዙ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ጥራት ያለው መረጃ ጥራት ያለው ውሳኔ ለማሳለፍ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡

ለዚህ ደግሞ የባለሙያዎችን አቅም ማሳደግ እና ወቅቱ የሚጠይቀውን ዕውቀት ማስታጠቅ ለነገ የማይባል ተግባር ነው ብለዋል፡፡

በመሆኑም አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ በአሁኑ ወቅት ዓለም አቀፍ ጥራት ያለው የስታትስቲክስ መረጃ ለመሰብሰብ፣ ለመተንተንና ለማሰራጨት ከተባባሪ አካላት ጋር በመሆን ሥልጠናዎችን በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ተግባሩን ቀጣይ ለማድረግ የሚያስችለውን የሥልጠና ማዕከል በማዘጋጀት ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከሥልጠናው በኋላ ለአገራዊ ፖሊሲ መነሻ የሚሆኑ የስታትስቲክስ መረጃዎችን በጥራት ለማመንጨት፣ለመተንተንና ለማሰራጨት ትልቅ ግብዓት እንደሚገኝበት ተጠቁሟል፡፡

ሥልጠናው ለተከታታይ ሦስት ቀናት እንደሚሰጥ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም