ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ቀጣናዊ የምግብ ዋስትናና የአካባቢ ጥበቃን ለማረጋገጥ የጀመረችውን ተምሳሌታዊ ተግባር አጠናክራ ትቀጥላለች-አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ

ጥቅምት 07 ቀን 2015 (ኢዜአ)  ኢትዮጵያ ቀጣናዊ የምግብ ዋስትናና የአካባቢ ጥበቃን ለማረጋገጥ የጀመረችውን ተምሳሌታዊ ተግባር አጠናክራ እንደምትቀጥል በጂቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ ተናገሩ።

የዓለም የምግብ ቀን በጂቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ፣ የጂቡቲ የግብርና ሚኒስትር መሐመድ አህመድ አዋሌህ፣ የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) ተወካዮችና ሌሎች እንግዶች በተገኙበት በተለያዩ መርሃ-ግብሮች ተከብሯል።

በመርሃ-ግብሩም ጂቡቲ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የጀመረቻቸው ተግባራትን የሚገልጹ ትዕይንቶች ቀርበዋል።

በዚሁ ወቅት  አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ እንዳሉት፤ የአፍሪካ ቀንድ በከባድ የአየር ንብረት ለውጥ እየተጠቃ ሲሆን፤ ድርቅና የበረሃ አንበጣም የቀጣናው የምግብ ዋስትና ላይ ከፍተኛ ስጋት መደቀናቸውን ጠቅሰዋል።

ከዚህም ባለፈ ዓለም አቀፍ ወረርሽኞችና የኃያላን አገራት ውጥረቶች ሌላ ተጨማሪ የቀጣናው ፈተና መሆናቸውን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማትና  የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ሥራዎች እያከናወነች መሆኗን ጠቅሰው፤በዚህም ዘላቂ የልማት ግቦችን የአፍሪካ 2063 አጀንዳን ለማሳካት የሚያስችሉ ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰዋል።

ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህም መንግሥት የአረንጓዴ አሻራን በጎረቤት አገራት በማስፋፋት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በስንዴ ምርትም ራሷን ከመቻል ባለፈ ለቀጣናው አገራት ለመላክ በዝግጅት ላይ መሆኗን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎችን ለማስፋፋትም ከቀጣናው አገራት ጋር በትኩረት እንደምትሰራ ጠቁመዋል።

የጂቡቲ የግብርና ሚኒስትር መሐመድ አህመድ አዋሌህ በበኩላቸው፤ የዘንድሮው የዓለም የምግብ ቀን  የተሻሉ ተሞክሮዎችን የምንቀምርበት ይሆናል።

በተለይ መልካም የግብርና ሥራዎችን ከምታከናውነው የኢትዮጵያ ልዑካን ጋር በቅንጅት መከበሩ ጥሩ አጋጣሚ ነው ብለዋል።

ጂቡቲ የሕዝቧን የምግብ ዋስትና ደህንነት ለማረጋገጥ ጥረት እያደረገች መሆኗን ጠቅሰው፤ በዚህ ሂደት የኢትዮጵያ አብሮነት ከልባችን የማይጠፋ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያዊያን ዘንድሮ ለጂቡቲ ከሰጡት ችግኝ ውስጥ ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ተክሎችም በመኖራቸው የጂቡቲ መንግሥትና ሕዝብ  ለኢትዮጵያ ታላቅ ምስጋና ማቅረቡን ጠቅሰዋል።

እነዚህ ችግኞችም ለጂቡቲ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ አጋዥ መሆናቸውን በመጠቆም።

ኢትዮጵያ በብዙ ዘርፍ ከጂቡቲ ጋር ጠንካራ ወዳጅነት እንዳላት ያነሱት ሚኒስትሩ፤ በተለይም ንጹህ የመጠጥ ውሃና ፍራፍሬ በማቅረብ ለጂቡቲ አለኝታ መሆኗን እያሳየች ነው ብለዋል።

በጂቡቲ የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት/ፋኦ/ አስተባባሪው ዶክተር ፋሎ ጉዬ በበኩላቸው፤ የጂቡቲ ሕዝብ በብዛት አርብቶ አደር  መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣናው ያለው ተፈጥሯዊ አደጋ ዋነኛ ተጠቂ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከእንስሳትና አሳ ሀብት ባሻገር በሰብል ምርትም ከጥገኝነት ለመላቀቅ እየተንቀሳቀሰች መሆኗን ጠቁመው፤ ከኢትዮጵያ ብዙ የግብርና ተሞክሮ መውሰድ እንደሚገባት አክለዋል።

የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት/ፋኦ/ በቀጣናው የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረጉ ተግባራትን እንደሚደግፍ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም