ቀጥታ፡

የህዳሴ ግድብ የአንድነታችን ማሰሪያ በመሆኑ የፖለቲካ ልዩነት ሳይገድበን ለፍጻሜ ለማብቃት በትብብር እንሰራለን - የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች

ጥቅምት 07 ቀን 2015 (ኢዜአ)  ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአንድነታችን ማሰሪያ በመሆኑ የፖለቲካ ልዩነት ሳይገድበን ለፍጻሜ ለማብቃት በትብብር እንሰራለን ሲሉ የተለያዩ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ፡፡

የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመገኘት የግንባታውን ሂደትና አሁናዊ ገጽታ ጎብኝተዋል።

ዶክተር መብራቱ ዓለሙ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ አበበ አካሉ የኢዜማ ዋና ጸሐፊና አቶ ዘሪሁን ገብረእግዚአብሔር የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር  በፓለቲካው ዘርፍ ያላቸውን ልዩነት በሰለጠነ መንገድ እየፈቱ የኢትዮጵያን ከፍታ በሚያረጋግጡ እንደ ህዳሴ ግድብ ባሉ የጋራ ልማቶች ላይ በትብብር መስራት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

"ግድቡ ከፖለቲካ በላይ የሆነ የአገር ሃብት ነው" ያሉት አመራሮቹ የነገዋን ኢትዮጵያ ዛሬ ለመገንባት መሰረት የሚጥል መሆኑንም ነው የገለጹት።

የፓለቲካ ፓርቲዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ ለሀገር አንድነት፣ ለሰላም መስፈንና ለልማት መረጋገጥ የበኩላቸውን እንደሚወጡም ቃል ገብተዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ከዕለት ጉርሱ ቀንሶ ለግድቡ ግንባታ ስኬት እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ አድንቀው በመንግስት በኩል የታየው ቁርጠኝነትም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

የኢትዮጵያዊያን አሻራ ያረፈበትን ታላቁን የኢትዮጵያን ህዳሴ ግድብ የመጎብኘት እድል በማግኘታቸው መደሰታቸውንም ገልጸዋል።

ልዩነቶችን ወደ ጎን ትቶ ብሄራዊ ምልክት በሆኑ ጉዳዮችና በአገር ልማት ላይ ማተኮር ከኢትዮጵያ አልፎ ቀጣናዊ ትስስርን ለመፍጠርም አስተዋጽኦው የጎላ እንደሆነ ተናግረዋል።

"ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የትውልድ ቅርስ ነው" ያሉት የፖለቲካ አመራሮቹ የህዳሴ ግድብ የገዢው ፓርቲ ወይም የመንግስት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሁላችንም በመሆኑ ግንባታውን በጋራ ማሳካት አለብን ብለዋል።

ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ባሻገር በሌሎች አገራዊ ፕሮጀክቶች ላይም የራሳቸውን አሻራ ለማሳረፍ ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ከእለት ጉርሱ ቀንሶ እያዋጣ ዛሬ ላይ ያደረሰው ግድብ ሃይል አመንጭቶ ለፍሬ መብቃቱን በአካል ተገኝተው ማረጋገጣቸው እንዳስደሰታቸውም ገልጸዋል።

ግድቡ ሙሉ በሙሉ እስኪጠናቀቅ ድረስም የኢትዮጵያ ህዝብ የተለመደ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በጉብኝቱ ከ50 በላይ የፓለቲካ ድርጅቶች የተውጣጡ የፓርቲ አመራሮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም