በገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ የተመራው የልዑካን ቡድን ከአይኤምኤፍ ዋና ዳይሬክተር ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያየ - ኢዜአ አማርኛ
በገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ የተመራው የልዑካን ቡድን ከአይኤምኤፍ ዋና ዳይሬክተር ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያየ
ጥቅምት 07 ቀን 2015 (ኢዜአ) በገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ የተመራው የልዑካን ቡድን ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ዋና ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጂኦርጂዬቫ ጋር የእዳ ሽግሽግን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውይይት አደረገ።
“በቀውሶች ወቅት አንድነት” በሚል መሪ ቃል ከመስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በአሜሪካ ዋሺንግተን ዲሲ ሲካሄድ የቆየው የአይኤምኤፍ እና ዓለም ባንክ ግሩፕ ዓመታዊ ስብሰባ ትናንት ተጠናቋል።
በገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ የተመራው ልዑካን ቡድን በስብስባው ላይ የሁለትዮሽና የባለ ብዙ ወገኖች ውይይት ላይ ተሳትፏል።
ልዑካን ቡድኑ ከአይኤምኤፍ ዋና ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጂኦርጂዬቫ ጋር የአይኤምኤፍ ጊዜያዊ የምግብ ፋይናንስ መርሐግብር የኢትዮጵያ ተጠቃሚነት እና የቡድን 20 የእዳ ሽግሽግ የጋራ ማዕቀፍ ዙሪያ ፍሬያማ ውይይት ማድረጉን በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታውቋል።
ቡድኑ በዋሺንግተን ዲሲ ቆይታው ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማትና የልማት አጋሮች ጋር ምክክር አድርጓል።
በአይኤምኤፍ እና ዓለም ባንክ ግሩፕ ዓመታዊ ስብሰባ የኢኮኖሚ ቀውስ፣ የምግብ ዋስትና፣ የምግብና ነዳጅ ዋጋ መናር፣ የትምህርት ኢንቨስትመንት፣ የሰው ሃብት ልማትና የአየር ንብረት ለውጥ ውይይት የተደረገባቸው ዋነኛ ጉዳዮች ናቸው።