ቀጥታ፡

አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ከዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማህበር የአፍሪካ ዳይሬክተር ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ

ጥቅምት 07 ቀን 2015 (ኢዜአ) በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ከዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማህበር የአፍሪካ ዳይሬክተር ፓትሪክ የሱፍ ጋር የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦትን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውይይት አደረጉ።

አምባሳደር ታዬ ከዳይሬክተሩ ጋር ማህበሩ በኢትዮጵያ በሚሰጣቸው ሁሉን አቀፍ አገልግሎቶች ዙሪያ መነጋገራቸውን በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መረጃ ገልጸዋል።

መንግስትና ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማህበር በኢትዮጵያ ሰብአዊ ድጋፍ ተደራሽ ለማድረግ እና በሰላም ሂደቱ የሚገኙ ለውጦችን ታሳቢ ያደረጉ አገልግሎቶችን ማሻሻል በሚቻልባቸው ጉዳይ በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ እንደሆኑ ተናግረዋል።

እ.አ.አ በ1863 የተቋቋመው ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማህበር እ.አ.አ ከ1977 ጀምሮ በኢትዮጵያ በሰብአዊ ድጋፍና አቅርቦት ላይ በመስራት ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም