ሀገራዊ ምክክር ሂደቱን ስኬታማ ለማድረግ የሶስትዮሽ የጋራ መግባቢያ ስምምነት ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክር ሂደቱን ስኬታማ ለማድረግ የሶስትዮሽ የጋራ መግባቢያ ስምምነት ተደረገ
ጥቅምት 07 ቀን 2015 (ኢዜአ) የሰላም ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት እና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሀገራዊ ምክክር ሂደቱን ስኬታማ ለማድረግ የሶስትዮሽ የጋራ መግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።
ስምምነቱን የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ፣ የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር ሄኖክ ፍስሀ እና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር አቡዱልቃድር አደም ተፈራርመዋል።
ስምምነቱ ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ የተሳካ እንዲሆን በትብብር ለመስራት የሚያስችል ነው ተብሏል።
በሦስቱ አካላት መካከል ሀገራዊ ምክክሩን አስመልክቶ የጋራ ግቦችን ከማስፈን አኳያ ትብብርንና መግባባትን ለመፍጠር ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል።
የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፤ ሁሉን አካታች ሀገራዊ ምክክር ለኢትዮጵያ ሰላምና ዴሞክራሲ መሰረት የሚጥል በመሆኑ ለዚህ ስኬት ሁሉም ሚናውን መወጣት አለበት ብለዋል።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር አብዱልቃድር አደም በሕዝብ ዘንድ ተስፋ ተጥሎበት የሚታየው አገራዊ ምክክር በመንግሥት እና በሕብረተሰቡ ላይ የሚታዩትን ዘርፈ- ብዙ ተግዳሮቶች ለመፍታት ያስችላል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር ሄኖክ መለሰ በበኩላቸው፤ በቅርበት እና በተጠናከረ መልኩ ሀገራዊ ምክክርን አስመልክቶ ከዚህ ቀደም ከነበረው አሰራር በተለየ መልኩ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የሦስትዮሽ የጋራ መግባቢያ ስምምነት ነው ብለዋል።