አክሲዮን ማህበሩ ለፈተናው ስኬት ተማሪዎችን በማጓጓዝ ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መሸፈኑን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
አክሲዮን ማህበሩ ለፈተናው ስኬት ተማሪዎችን በማጓጓዝ ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መሸፈኑን አስታወቀ

ጭሮ ፣ጥቅምት 6/2015 (ኢዜአ)- የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር አክሲዮን ማህበር ለሁለተኛው ዙር የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ስኬታማነት ተማሪዎችን በማጓጓዝ ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መሸፈኑን አስታወቀ።
አክሲዮን ማህበሩ 1ሺህ 191 የ12ኛ ክፍል የተፈጥሮ ሳይንስ ተፈታኝ ተማሪዎችን ትላንት ከሚኤሶ ባቡር ጣቢያ ወደ ድሬደዋ ዩኒቨርስቲ አጓጉዟል፡፡
ከተፈታኝ ተማሪዎች መካከል ሁለት መንትያ ወንድማማቾችና አንድ ጎልማሳ የሀይማኖት አባት ፈተናውን በራሳቸው እውቀት ለመስራት ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር አክሲዮን ማህበር ቺፍ ኦፕሬሽን ኦፊሰር አቶ ተሾመ እሸቴ በሽኝት ስነ ስርዓቱ ላይ እንደገለጹት ምድር ባቡር ተፈታኝ ተማሪዎችን በማጓጓዝ ድጋፍ ያደረገው ተፈታኞች ሰላማዊና ደህንነቱ በተጠበቀ ጉዞ ወደ መፈተኛ ቦታቸው ደርሰው በተረጋጋ መንፈስ ለፈተና እንዲቀርቡ በማሰብ ነው።
እንዲሁም የፈተናው ሂደት ስኬታማ ሆኖየታለመለትን ግብ እንዲመታ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠርና አስተዋጾ ለማድረግ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
“አክሲዮን ማህበሩ በዚህ ጉዞ ብቻ ከ1 ሚሊዮን በላይ ወጪ ሸፍኗል “ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
“ተፈታኞች ሀገርን በሚያኮራ ስነምግባርና የፈተና ውጤት እንደሚክሱን ተስፋ እናደርጋለን” ሲሉም መልእክት አስተላልፈዋል ፡፡
በጉዞው ሽኝት ከተደረገላቸው ተፈታኝ ተማሪዎች መካከል መንትያ ወንድማማቾች የተገኙ ሲሆን ፈተናውን በራሳቸው እውቀትና ጥረት ለመስራት ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል ።
የሁለት ደቂቃ የእድሜ ልዩነት ያላቸው መንትያ ወንድማማቾች አክለው ተማሪዎች የሚሄዱበትን አላማ ዘንግተው ምክንያቱ በማይታወቅ ችግር ሰለባ ሊሆኑ እንደማይገባ መክረዋል፡፡

ተማሪ ዮናታን ቴዎድሮስ “ተማሪዎች ራሳቸውን መጠበቅ ያለባቸው ለራሳቸው ብቻ ብለው ሳይሆን ለቤተሰባቸውና ለሀገራቸው ጭምር ነው” ብሏል፡፡
“ተማሪዎች በምንም ነገር አላማቸውን መዘንጋት የለባቸውም” ያለው ተማሪ ዮናታን ተማሪዎች ለፈተናው የተቀመጠን መመሪያ በመተግበር ለሰላማዊነቱ ሀላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል” ብሏል።
መንትያ ወንድሙ ተማሪ አቤንያ ቴዎድሮስ በበኩሉ “በዋናነት ከእኛ የሚጠበቀው ፈተናውን እሰራዋለሁ ብለን ወደ ተነሳንበት አላማ መሄድና ግቡን አሳክተን መመለስ ብቻ ነው” ብሏል፡፡
ፈተናውን በስኬት በመወጣት ወደ ዩኒቨርስቲ በመግባት ሀገርንና ቤተሰቦቻችንን ተጠቃሚ ለማድረግ መዘጋጀቱን አስታውቋል።
በሌላ በኩል “ከቤተክህነት አገልግሎት ጎን ለጎን መደበኛ ትምህርት ተምሬ የዩኒቨርስቲ መግቢያ ላይ ደርሻለሁ" ያሉት ደግሞ የሁለተኛ ዙር የ12ተኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ተፈታኝና የ41 አመቱ ጎልማሳ የሀይማኖት አባት ናቸው ፡፡
በምዕራብ ሀረርጌ ዞን አንጫር ወረዳ ነዋሪ የሆኑት ቀሲስ አብይ ንጉሴ ተስፋ ከስብከተ ወንጌልና ቅስና አገልግሎት ጎን ለጎን በደይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመደበኛው ክፍለ ጊዜ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡
ትላንት ከሚኤሶ ባቡር ጣቢያ ወደ ድሬደዋ ዩኒቨርስቲ ከተጓዙ ከምዕራብ ሀረርጌ ዞን የተውጣጡ ተማሪዎች አንዱ ሆነው በመሸኘታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡
“እኔን የሚመለከቱና አብረውኝ የሚማሩ ከእኔ መልካም ተሞክሮን እንደሚማሩ እየተገነዘብኩ በመምጣቴ በፅናት ተምሬ እዚህ ደርሻለሁ “ ብለዋል፡፡
በፈተናው የተሻለ ውጤት አምጥተው ወደ ዩኒቨርስቲ የመግባት ህልም እንዳላቸውና ሀገራቸውን በሀይማኖታዊ አገልግሎቱም ሆነ በተማሩበት ትምህርት የማገልገል ከፍተኛ ተነሳሽነት እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡