ቀጥታ፡

ከቡራዩ የተፈናቃሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን የከተማው ነዋሪዎቸ ገለፁ

ቡራዩ  መስከረም 12/2011  ከቡራዩና አካባቢው  የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም  ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን የቡራዩ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ። ነዋሪዎቹ ዛሬ ባካሄዱት የሰላም ኮንፈረንስ ላይ እንደተናገሩት ባለፈው ሳምንት በሚኖሩበት አካባቢ የተፈጠረው ክስተት እነርሱን የማይወክል ሌላ ተልእኮ ያላቸው ኃይሎች የፈፀሙት እኩይ ተግባር ነው። ይህ ድርጊት በበርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች ላይ የሞት፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመትና የመፈናቀል አደጋ ያስከተለ ሲሆን፤ ከዚህ ተግባር ጀርባ ያሉት ወንጀለኞች ተገቢውን የፍርድ ቅጣት እንዲያገኙ መደረግ እንዳለበትም የከተማዋ ነዋሪዎች አሳስበዋል። ነዋሪዎቹ አክለውም የተፈናቀሉትን ከማቋቋም ባሻገር በአካባቢው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ከሚመለከታቸው የመንግስትና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተቀራርበው ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል። በከተማውና አካባቢው ተመሳሳይ ችግሮች እንዳይከሰቱ ለማድረግ በሚያስችሉ ዝግጅቶች ላይም ነዋሪዎቹ ተወያይተዋል። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተር ያነጋገራቸው የውይይቱ ተሳታፊዎችም በከተማዋ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እና ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም የተለያዩ ስራዎች እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል። ወይዘሮ እንግዳወርቅ በቀለ  "የተጠቁት ጎረቤቶቼ ናቸው፣ ወንድሞቼ ናቸው፣እህቶቼ ናቸው፣ ሁላችንንም አብረነው የምንኖረው። የእነርሱ መፈናቀል ግን ሁላችንንም ነው የጎዳው። ውስጣችንን አሳምሞናል።"  ብለዋል አቶ ከዲር ሳዲቅ  ደግሞ  የችግሩ ተጋላጭ  እንደነበሩ  አመላክተው  የአካባቢው ህብረተሰብ  ከለላ እንደሰጣቸው ተናግረዋል፡፡  ከዚህ በፊት  ህብረተሰቡ  ተከባብሮ  በሰላም  እንደሚኖር  አመላክተው  የተፈጸመው ተግባርየኦሮሞን  የአካባቢውን  ህዝብና  ቄሮንም  እንደማወክል   የተናገሩት  ድግሞ አቶ ተስፋዬ ብዙአየሁ ናቸው፡፡  ህብረተሰቡ  የጠፈናቀሉ ሰዎች  እንዲመለሱ፣ ቤታቸውን በማደስ   አጥራቸውን  በመጠገን  ድጋፍ እደረገ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡  የቡራዩ ከተማ ከንቲባ አቶ ሰለሞን ፈዬ በበኩላቸው እንዳሉት የድርጊቲ ፈጻሚዎች ታይዘው ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑን ገለፀው፤ ተፈናቃኖች ወደቤታቸው እንዲመለሱ የተለያየ ስራ በመከናወን ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል። በዚህም የተወሰኑት ወደቀዬአቸው መመለስ መጀመራቸውን ገልፀዋል። የተዘረፉ ንብረቶችን ለማስመለስም ከፀጥታ አካላት ጋር እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።  በቡራዩና አካባቢዋ በተፈጸመው ድርጊት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች በተለያየ መንገድ ድጋፍ እየተደረገላቸው ሲሆን፤ ተፈናቃዮቹ ወደ አካባቢያቸው ተመልሰው ኑሯቸውን የሚጀምሩበት መንገድ እየተመቻቸ መሆኑ እየተዘገበ ይገኛል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም