ቀጥታ፡

የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጎበኙ

ጥቅምት 6/2015 (ኢዜአ) የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመገኘት የግንባታውን ሂደትና አሁናዊ ሁኔታን ጎብኝተዋል።

የህዳሴ ግድቡን የጎበኙት አገራዊ እና ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ናቸው።

የኢትዮጵያዊያን አሻራ ያረፈበትን ታላቁን የኢትዮጵያን ህዳሴ ግድብ የመጎብኘት እድል በማግኘታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

አመራሮቹ በፓለቲካው ዘርፍ ያላቸውን ልዩነት በሰለጠነ መንገድ እየፈቱ እንደ ህዳሴ ግድብ ባሉ የአገርን ዕድገት የሚያፋጥኑ የጋራ ልማቶች ላይ በትብብር መስራት ይኖርብናልም ብለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት የዴሞክራሲ ስርአት ማስተባበሪያ ማዕከል አስተባባሪ ዶክተር አለሙ ስሜ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያውያን ትብብር እና አንድነት በመገንባት ላይ ያለ የጋራ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋለ።

የግድቡን ግንባታ ከዳር ለማድረስ የሁሉም ትብብርና ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን አመላክተዋል።

የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ ለማደናቀፍ የሚሰሩ ሃይሎችን በጋራ ልንመክታቸው ይገባልም ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ የፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶክተር መብራቱ ዓለሙ የግድቡኑ ገጽታና ስራ በቦታው ተገኝተው በመጎብኘታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

የፓለቲካ ፓርቲዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ ለሀገር አንድነት፣ ሰላምና ልማት መፍጠን የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

ለአገር ብልጽግና፣ አንድነትና ልማት መሰረት የሆነው የህዳሴ ግድብ ግንባታ በስኬት እንዲጠናቀቅ የሁሉም ድጋፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

በጉብኝቱ ከ50 በላይ የፓለቲካ ድርጅቶች የተወጣጡ የፓርቲ አመራሮች ተሳትፈዋል።

ለፓርቲ አመራሮቹ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን እና የክልሉ ከፍተኛ የስራ አመራሮች በአሶሳ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም