ቀጥታ፡

የሉዓላዊነት፣ የነጻነትና ምልክት በሆነው ሰንደቅ ዓላማ ስር ተሰባስበን የኢትዮጵያን ህልውና ጠብቀን ልናስቀጥል ይገባል

ጥቅምት 6/2015 (ኢዜአ) የሉዓላዊነት፣ የነጻነትና የአንድነት ምልክት በሆነው ሰንደቅ ዓላማ ስር ተሰባስበን የኢትዮጵያን ህልውና ጠብቀን ልናስቀጥል ይገባል ሲሉ የፖሊስ አባላት ገለጹ።

ለ15ኛ ጊዜ የሚከበረው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በነገው እለት በተለያዩ መርሃ ግብሮች ይከበራል።

የአፍሪካ የነፃነት ተምሳሌትና የብሔራዊ አንድነት መገለጫ የሆነው ታሪካዊው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በሚገባው ክብር ልክ ማክበር የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን በርካቶች ይናገራሉ።

በዚሁ ዙሪያ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ የትራፊክ ፖሊስ አባላት የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ የአፍሪካ ኩራትና የነፃነት ተምሳሌት በመሆኑ ታላቅ ክብር ሊሰጠው እንደሚገባ ገልጸዋል።

በኮሚሽኑ የትራፊክ አደጋ የህዝብ ግንዛቤ ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ዳዊት ሙሉጌታ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ የነፃነትና አሸናፊነት ምልክት በመሆኑ ትውልዱ ሊኮራበት ይገባል ብለዋል።

በዓለም አደባባይ በተለያዩ መድረኮች አትሌቶች አሸንፈው በደስታ የሚያነቡለትና ለአገራቸው ክብር ሲሉ የሚዋደቁለት የድል ተምሳሌት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በሰላም ማስከበር ተልዕኮ አርማውን አንግበው የሚሰማሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች ተከብረውና አስከብረው የሚመለሱትም በሰንደቅ አላማ ታጅበው መሆኑን በመጥቀስ።

በመሆኑም በእነዚህና ሌሎች በተምሳሌትነት ለሚነሳውና ለሚታወሰው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ክብር ሲባል መስዋዕትነት መክፈል የሚያኮራ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።

"ሰንደቅ ዓላማና አገር የተሳሰሩ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች" ናቸው ያሉት ምክትል ኢንስፔክተር ዳዊት፤ የሉዓላዊነት፣ የነጻነትና የአንድነት ምልክት በሆነው ሰንደቅ ዓላማ ስር ተሰባስበን የኢትዮጵያን ህልውና ጠብቀን ልናስቀጥል ይገባል ብለዋል።

በሰንደቅ አላማ ዙሪያ የወጣው ህግ በሁሉም ዜጎች ተግባራዊ ሆኖ በትውልድ ቅብብሎሽ የሚገባው ክብር ልክ እየተከበረ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ ጠቅሰዋል።

በሁሉም ተቋማት በትምህርት ቤቶችና አጠቃላይ በህዝቡ ዘንድ ሰንደቅ ዓላማ ተገቢው ቦታና ክብር ሊሰጠው ይገባልም ነው ያሉት።

የኮሚሽኑ የትራፊክ ባለሙያ ረዳት ሳጅን ማንጠግቦሽ አበበ፤ የአገርን ሰንደቅ አላማን ማክበር ራስን ማክበር በመሆኑ ሁላችንም ለክብራችን በጋራ መቆም አለብን ብለዋል።

በትምህረት ቤቶችም ይሁን በተለያዩ ተቋማት ለሰንደቅ ዓላማ ክብርና ጥንቃቄን ማድረግ ልምድ ሆኖ መቀጠል አለበትም ነው ያሉት።

የዘንድሮው ሰንደቅ ዓላማ ቀን "ሰንደቅ ዓላማችን የብዝሃነታችን መገለጫ፤ የሉዓላዊነታችን ምሰሶ" በሚል መሪ ሃሳብ ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም