ቀጥታ፡

የአፋር እና አማራ ክልል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ይበልጥ ለማጠናከር በቅንጅት እየተሰራ ነው

ከሚሴ (ኢዜአ) ጥቅምት 6/2015----- የአፋር እና የአማራ ክልል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ይበልጥ ለማጠናከርና በልማት ለማስተሳሰር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የአፋር ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አስታወቁ።

በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞንና የአፋር ክልል የጋራ የሰላም የምክክር መድረክ በከሚሴ ከተማ ተካሄዷል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ ሐጅ ቢላይ አህመድ እንደተናገሩት፣ የሁለቱ ክልል ህዝቦች በባህል፣ በታሪክ፣ በጋብቻና በሌሎችም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሮች የተሳሰሩ ህዝቦች ናቸው።

ይህን ታሪክ የማይሽረውን የአብሮነት፣ የጋራ ባህልና እሴት ባልተገቡ ትርክቶች በመሸርሸር የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚሰሩ የጥፋት ሀይሎች መኖራቸውን ገልጸዋል።

"የሁለቱም ክልል ህዝብ ሰላምና ልማት ፈላጊ በመሆኑ በጥፋት ሀይሎች በተደጋጋሚ የሚሰሩ ሴራዎችን በጋራ በማክሸፍ አንድነቱንና ሰላሙን አጠናክሮ ቀጥሏል" ብለዋል።

ሁለቱን ክልሎች ባለድርሻ አካላትን ጭምር በማስተባበር በህዝቦች መካከል የእርስ በእርስ ግንኙነትን ለማጠናከርና ለጋራ ልማት ተጠቃሚነት በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ ቀጠናውን በትምህርት፣ በመጠጥ ውሃ፣ በመስኖ፣ በገበያና በሌሎችም እንቅስቃሴዎች በማስተሳሰር በጋራ የልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ እየተሠራ ያለውን ሥራ በማሳያነት ጠቅሰዋል።

በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ አሊ በበኩላቸው "የአዋሳኝ አካባቢዎችን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በማጠናከር ቀጠናውን በልማት ለማስተሳሰር እየተሰራ ነው" ብለዋል።

ህዝቦችን በመሰረተ ልማት በማስተሳሰር የአባቶቻችንን የቀደመ የመተጋገዝ፣ የመረዳዳትና የአብሮነት ባህልና እሴቶች እናጎለብታለን ሲሉም አክለዋል።

እንደ አስተዳዳሪው ገለጻ በአሸባሪዎቹ ሸኔ እና ህወሓት በአካባቢው በተደጋጋሚ የተቃጣውን የጥፋት ሴራ ህብረተሰቡ በአብሮነት ባህሉ አክሽፎ አንድነትና ሰላሙን እያስቀጠለ ይገኛል።

"የአማራ እና የአፋር ህዝቦች ላይለያዩ በባህል፣ በጋብቻና በተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሮች የተሳሰሩ ናቸው" ያሉት ደግሞ በአፋር ክልል የዞን 5 ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ ማቴ ናቸው።

የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን በማጠናከር ለጋራ ልማትና ተጠቃሚነት በቅንጅት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

በአዋሳኝ አካባቢዎች አልፎ አልፎ በግጦሽ፣ በእርሻ መሬት፣ በእንስሳት መጥፋትና በሌሎችም ምክንያቶች የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን እንደቀደሙት አባቶቻችን በውይይት፣ በሽምግልና እና እርቅ በመፍታት በቀጠናው ዘላቂ ሰላም እየተፈጠረ መሆኑን አስረድተዋል።

የህዝብን አንድነትና ሰላም በመጠበቅ ቀጠናዊ የልማት ትስስሩ እንዲጎለብት የድርሻችንን እንወጣለን'' ያሉት ደግሞ በአፋር ክልል የሀደልኤላ ወረዳ የሃይማኖት አባት ሸህ አሊ ኢብራሂም ናቸው።

"በእምነትና በብሔር ስም ሁከትና ብጥብጥ በመፍጠር አካባቢውን የስጋት ቀጠና ለማድረግ የሚሰሩ የደም ነጋዴዎችን አጋልጠን ለህግ በማቅረብ የበኩላችንን እንወጣለንም" ብለዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ የክልል፣ የዞንና ወረዳ አመራሮች እንዲሁም የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የጎሳ መሪዎች፣ አባ ገዳዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም