ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የጀግንነትና የአፍሪካ የነፃነት ተምሳሌት የሆነውን ሰንደቅ አላማ ተገቢውን ክብር ልንሰጠው ይገባል- የመዲናዋ ነዋሪዎች

ጥቅምት 6/2015/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ የጀግንነትና የአፍሪካ የነፃነት ተምሳሌት የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ የሚገባውን ክብር ልንሰጠው ይገባል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የአፍሪካ የነፃነት ተምሳሌትና የብሔራዊ አንድነት መገለጫ ተደርጎ የሚታይ መሆኑ ይታወቃል።

የብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል በተለያየ መልኩ በየአመቱ እየተከበረ የቆየ ሲሆን፤ዘንድሮም ለ15ኛ ጊዜ በነገው እለት ይከበራል። 

ሰንደቅ ዓላማችን የመስዋዕትነት፣ የሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነት፣ የስነ-ልቦና፣ የፖለቲካ ታሪክ፣ የአብሮነትና የብሔራዊ መግባባት መገለጫ አርማ ምልክታችን በመሆኑ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ለሰንደቅ ዓላማ የሚገባውን ክብር መስጠት፤ የማክበርና የማስከበር ሃላፊነትና ግዴታ አለበት ሲል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የበዓሉን አከባበር ሥነ ሥርዓት ባሳወቀበት መግለጫው መጠቆሙም ይታወሳል።

የሰንደቅ ዓላማ ቀንን ተገቢውን ክብርና የአገር ፍቅር እንዲሁም አብሮነትን በሚያሳይ መልኩ ለማክበር መዘጋጀታቸውን ኢዜአ ያነጋገረቸው የመዲናዋ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑት ሻምበል  ኑርልኝ ገብረኪዳን፤ የገዘፈ ታሪክና ታላቅ ክብር ያለውን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በሚገባው ልክ ማክበር የሁላችንም ግዴታ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

ጀግኖች አባቶቻችን ለሰንደቅ አላማ እና ለአገራቸው ክብር ሲሉ በጀግንነት መስዋእትነት የከፈሉበት በመሆኑ ይህንን ክብር ሰጥቶ ማስቀጠል ደግሞ ተገቢ ነው ይላሉ።

በመሆኑም የኢትዮጵያ የጀግንነትና የአፍሪካ የነፃነት ተምሳሌት የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ የሚገባውን ክብር ልንሰጠው ይገባል ብለዋል።

እለቱን ስናከብርም ኢትዮጵያ በሁሉም መስኮች የጀመረቻቸውን የልማት ሥራዎች ከግብ ለማድረስ በመዘጋጀት መሆን አለበት ነው ያሉት።

የአዲስ አበባ ፖሊስ አባል ኢንስፔክተር ረታ አበበ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ዘመን ተሻጋሪ ታሪክ ፤ በነጻነቷ የምትጠቀስና የገዘፈ ታሪክ ያላት በመሆኗ ከዚህ ታሪክ ጋር የማይነጣጠለውን ሰንደቅ ዓላማ ተገቢውን ክብር ልንሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡

የሰንደቅ ዓላማ ቀንን  ስናከበር ደግሞ በጋራ ቆመን የቀደመውን የነጻነት ታሪካችንን በመዘከርና ኢትዮጵያ የጀመረቻቸውን ሁለንተናዊ ልማት በማስቀጠል መሆን አለበት ነው ያሉት።

የዘንድሮው የብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ በዓሉ “ሰንደቅ አላማችን የብዙሃነት መገለጫ፤ የሉአላዊነታችን ምሰሶ ነው” በሚል መሪ ሃሳብ በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሪነት በመላው ሀገሪቱ የሚከበር ሲሆን፤ በፌደራል የመንግስት ተቋማት፣ በክልሎችና በሁለቱም ከተማ አስተዳደሮች፣ በመከላከያ ሰራዊት ካምፖች እንዲሁም በኢምባሲዎችና የኢትዮጵያ ሚሲዮኖች በተመሳሳይ ሰዓት ከረፋዱ 4፡30 ላይ ሰንደቅ ዓላማ በመስቀልና በሰንደቅ ዓላማ ፊት ቃለ መሐላ በመፈፀም ስነ-ስርዓት እንዲሁም በተለያዩ ዝግጅቶች በደማቅ ሁኔታ የሚከበር ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም