ቀጥታ፡

ኢንተርፕራይዙ የምርጥ ዘር አቅርቦት እጥረትን ለማቃለል እያደረገ ያለው ጥረት ተስፋ ሰጪ ነው---ባለድርሻ አካላት

ጎባ (ኢዜአ) ጥቅምት 6/2015---የኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ በምርጥ ዘር ፍላጎትና አቅርቦት ላይ ያለውን ክፍተት ለማቃለል እያከናወነ ያለው ተግባር ተስፋ የሚጣልበት መሆኑን የተለያዩ የግብርና ባለድርሻ አካላት ገለጹ።

በኢንተርፕራይዙ የባሌ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ይዞታ ሥር ያሉ የተለያዩ የምርጥ ዘር ማባዣ ማሳዎች ተጉብኝተዋል።

በመስክ ምልከታው ላይ የተሳተፉት የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ፈቶ ኢስሞ እንዳሉት በምርምር ተቋማት የሚወጡ አዳዲስ የሰብል ዝርያዎች ለአርሶ አደሩ ሊደርሱ ይገባል፡፡

"ዝርያዎቹ በስፋት ተባዝተው አርሶ አደሩ ዘንድ እንዲደርሱ በማድረግ በኩል ኢንተርፕራይዞች እንደ  ድልድይ ሆነው ያገለግላሉ" ብለዋል።

የኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ በክልሉ ብሎም በአገሪቱ የሚታየውን የምርጥ ዘር ፍላጎትና የአቅርቦት አለመጣጣም ችግር ለመፍታት እያከናወነ ያለው ሥራ የሚደነቅ መሆኑን በጉብኝቱ ወቅት መመልከታቸውን ገልጸዋል።

"ኢንተርፕራይዙ የምርጥ ዘር ፍላጎትን ከማሟላት በተጓዳኝ በመንግስት የተያዘውን ስንዴን በስፋት የማልማት ግብ እንዲሳካ እያደረገ ያለው ጥረት ተስፋ የሚጣልበት ነው" ያሉት ደግሞ የኦሮሚያ ግብርና ምርምር ኢኒስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ለማ አበራ ናቸው።

የምርጥ ዘር የሚያፈልቁና ዘሩን በስፋት በማባዛት አርሶ አደሩ ዘንድ የሚያደርሱ ኢንተርፕራይዞች መካከል ያለው ግንኙነት መጠናከር በግብርናው ዘርፍ ለተቀመጠው አገራዊ ግብ ስኬት ውጤታማነት ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አስረድተዋል።

በኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ የባሌ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ጫላ አበባ በበኩላቸው እንዳሉት፣ ኢንተርፕራይዙ በዋናነት የአርሶ አደሩን የምርጥ ዘር ፍላጎት ለማሟላት በትኩረት እየሰራ ነው።

ኢንተርፕራይዙ በ2014/15 የምርት ወቅት ከ17 ሺህ በሚበልጡ ማሳዎች ላይ እያባዛ ካለው የተለያዩ የምርጥ ዘር አይነቶች ከግማሽ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱንም ጠቁመዋል።

ከተለያዩ የግብርና ምርምር ማዕከላት ተገኝተው በኢንተርፕራይዙ እየተባዙ ከሚገኙ ምርጥ ዝርያዎች መካከል የዋግ በሽታን በመቋቋም የተሻለ ምርት የሚሰጡ የስንዴ፣ ገብስ እና የባቄላ ዝርያዎች እንደሚገኙበት ገልጸዋል።

ዶክተር አሽኔ እንዳሉት ኢንተርፕራይዙ የምርጥ ዘር ፍላጎትን ለማሟላት ከሚያደርገው ጥረት በተጓዳኝ መንግስት የያዛቸውን ስንዴን በመስኖ የማልማትና ወደውጪ የመላክ ግብ እንዲሳካ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑንም አመልክተዋል።

በተለይ በመስኖ ስንዴ የምርጥ ዘር እጥረት እንዳያጋጥም በኢንተርፕራይዙ ተመርተው የተበጠሩ ከ80 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘሮች ለአርሶ አደሮች እየተሰራጩ መሆኑን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

የኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ በ2014/2015 የምርት ወቅት በአጠቃላይ እየለማ ካለው ከ34 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት ላይ 1 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ከኢንተርፕራይዙ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የምርጥ ዘር ልማቱም በኢንተርፕራይዙ፣ በአርሶ አደርና በባለሀበት መሬት ላይ ጭምር እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ከምዕራብ አርሲ ዶዶላ ወረዳ አርሶ አደሮች መካከል ጁላ ዋቤ በሰጡት አስተያየት ምርጥ ዘር በወቅቱና በሚፈልጉት መጠን ማግኘታቸው ምርታማነታቸውን እንዲጨምር አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢንተርፕራይዙ ከሚያደርግላቸው የምርጥ ዘር ድጋፍ በተጨማሪ በሌሎች የግብርና ቴክኖሎጂዎች አጠቃቀም ላይ ሙያዊ ስልጠና እየሰጣቸው መሆኑን የገለጹት ደግሞ አርሶ አደር ሀሰን ከድር ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም