ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ጂቡቲ በጋራ ለመልማት የያዟቸውን እቅዶች ለማሳካት በቁርጠኝነት ይሠራሉ- የአገራቱ ከፍተኛ አመራሮችና ወጣቶች

ጥቅምት 6/2015/ኢዜአ/ ኢትዮጵያና ጂቡቲ የጀመሯቸውን በጋራ የመልማት እቅዶች ለማሳካት በቁርጠኝነት ይሠራሉ ሲሉ የአገራቱ ከፍተኛ አመራሮችና ወጣቶች ተናገሩ።

የኢትዮጵያና የጂቡቲን ታሪካዊ ወዳጅነት ማጠናከር ያለመ የወጣቶች የህዝብ ለህዝብ የትውውቅ መድረክ ትናንት ምሽት በጂቡቲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲተካሂዷል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የሁለቱም አገሮች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ አምባሳደሮች፣ ወጣቶች እና የማህበረሰብ ተወካዮች ተገኝተዋል።

በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ፅሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ሀሰን አብዱለቃድር፤ ኢትዮጵያ አገራዊ ችግሮቿን በራሷ አቅም ለመፍታትና ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማምጣት እየሠራች ነው ብለዋል።

በዚህ የኢትዮጵያ የልማት ጉዞ ዓለም አቀፋዊ ተፅዕኖ እየፈጠረ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋምን ያለመ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አንዱ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ይህንን ተሞክሮዋን ለጎረቤቶቿና ለመላው አፍሪካውያን ለማስፋፋት እየሰራች መሆኗንም ጠቅሰዋል።

ተሞክሮን ከማስፋት ባለፈ በጂቡቲ በሦስት ዙር ከ250 ሺህ በላይ ችግኞችን በመትከል የሁለቱን አገራት ሁሉን አቀፍ ወዳጅነት ይበልጥ የሚያስተሳስር ሥራ ተጠናክሮ ይሠራል ብለዋል።

የኢትዮጵያና የጂቡቲ ወጣቶች የሁለቱን አገሮች ወዳጅነት በቀጣይም በአዳዲስ ዘርፎች አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉ አረጋግጠዋል።

የጂቡቲ የግብርና ሚኒስትር መሐመድ አህመድ አዋሌህ በበኩላቸው፤ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በፅኑ መሰረት ላይ የተገነባ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ  ዓለምን እየጎዳ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም ጂቡቲንም የአረንጓዴ ልማት አሻራ መርሃ ግብሯ ውስጥ በማካተቷ መቼም የማንረሳው ትልቅ ስጦታ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያና የጂቡቲ ወጣቶች መጪው ዘመን የእነሱ መሆኑን አውቀው፤ አንድታቸውን በማጠናከር ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋን በጋራ ሊከላከሉ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

በጂቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ፤ ኢትዮጵያ የፀረ ቅኝ አገዛዝ ትግልን በማቀጣጠል አፍሪካውያን በአንድነት በመነሳት ነጻነታቸቸውን እንዲቀዳጁ ጉልህ ሚና ማበርከቷን ጠቅሰዋል።

የዚህ ዘመን አፍሪካውያን መሪዎች ፓን አፍሪካኒዝምን በአረንጓዴ ልማት ለመድገም መነሳታቸውን ገልጸው፤ ኢትዮጵያም ፈር ቀዳጅ መሆኗን ተናግረዋል።

አፍሪካውያን ወጣቶች የዚህ ዘመን አፍርካዊ ወንድማማችነት የማጠናከር ኃላፊነት እንደተጣለባቸውም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያና የጂቡቲ ወጣቶች እንዲሁም መላው ህዝብ የሁለቱን ሀገራት የዘመን ተሻጋሪ የጋራ ራዕይ እውን ከማድረግ የሚያስቆማቸው የለም ብለዋል።

በመድረኩ ላይ ልምዳቸውን ያካፈሉት የኢትዮጵያና የጂቡቲ ወጣቶች፤ የሀገራቱን መጪ ዘመን  የተሻለ ለማድረግ በትጋት እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።

በተለይም አፍሪካዊ ወንድማማችነትን ለማጽናት ከምንጊዜውም በላይ ጫናዎችን በጋራ መመከት እንደሚገባና የወደፊት የጋራ እጣ ፈንታን ለማሳካት እጅ ለእጅ ተያይዞ የመነሻው ጊዜ አሁን ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም