ቀጥታ፡

ለኢትዮጵያ ሉአላዊነትና ለሰንደቋ ክብር ስንል ሁሌም በጀግንነት መስዋእትነት ለመክፈል ተዘጋጅተናል- የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት

ጥቅምት 6/2015/ኢዜአ/ ለኢትዮጵያ ሉአላዊነትና ለሰንደቋ ክብር ስንል ሁሌም በጀግንነት መስዋዕትነት ለመክፈል ተዘጋጅተናል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ተናገሩ፡፡

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የአፍሪካ የነፃነት ተምሳሌትና የብሔራዊ አንድነት መገለጫ ተደርጎ የሚታይ መሆኑ ይታወቃል።

ለዚህም በአገር አቀፍ ደረጃ የሰንደቅ ዓላማ ቀን መከበር የጀመረ ሲሆን ዘንድሮም ለ15ኛ ጊዜ በነገው እለት የሚከበር ይሆናል።

እለቱን የሰንደቅ ዓላማችንን ክብርና የኢትዮጵያን ታላቅነት በሚያሳይ መልኩ በአብሮነት ለማክበር ተዘጋጅተናል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ገልጸዋል።

ለኢትዮጵያ ሉአላዊነትና ለሰንደቋ ክብር ስንል ሁሌም በጅግንነት መስዋእትነት ለመክፈል ተዘጋጅተናል ሲሉም የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላቱ አረጋግጠዋል።

ካነጋገርናቸው የሰራዊት አባላት መካከል አስር አለቃ አየነው አባይ፤ ለሃገር ቀጣይነት የኢትዮጵያን ዳርድንበር ለማስከበርና ለሰንደቋ ክብር በመቆም ሰራዊቱ በጀግንነት መስዋዕትነት እየከፈለ መሆኑን ተናግረዋል።

የአንድ አገር ታላቅነትና ፍቅር የሚገለጽበት ታላቅ ምልከት ለሆነው ሰንደቅ ዓላማ የሚከፈል መስዋእትነት ኩራት በመሆኑ ሁላችንም ለዚሁ ዝግጁ ነን ብለዋል።

ከሰራዊቱ አመራሮች መካከል ሻለቃ ተመስገን ዮሀንስ በበኩላቸው፤ ሀገር እና ሰንደቅ አላማ የማይነጣጠሉ የክብርና አንድነት መገለጫዎች መሆናቸውን ይናገራሉ።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት ለሰንደቁ ክብርና ለሀገሩ ፍቅር ሲል በጀግንነት መስዋእትነት እየከፈለ መሆኑንና በቀጣይም ለዚሁ ዝግጁ መሆኑን የተናገሩት ምክትል አስር አለቃ ብርሀን ዳኙ ናቸው፡፡

የዘንድሮው ሰንደቅ ዓላማ ቀን "ሰንደቅ ዓላማችን የብዝሃነታችን መገለጫ፤የሉዓላዊነታችን ምሰሶ" በሚል መሪ ሃሳብ ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም