በጂቡቲ የተካሄደው የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር የሁለቱን አገራት የጠበቀ ወዳጅነትን በአረንጓዴ ልማት የሚያስተሳስር ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጂቡቲ የተካሄደው የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር የሁለቱን አገራት የጠበቀ ወዳጅነትን በአረንጓዴ ልማት የሚያስተሳስር ነው
ጥቅምት 05 ቀን 2015 (ኢዜአ) በጂቡቲ የተካሄደው የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር የሁለቱን አገራት የጠበቀ ወዳጅነትን በአረንጓዴ ልማት የሚያስተሳስር መሆኑን የኢትዮጵያና የጂቡቲ ወጣቶች ገለፁ።
የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዲፕሎማሲ የወጣቶች ልዑክ እና የጂቡቲ ወጣቶች የአፍሪካ ወንድማማችነትን ለማጠናከር ያለመ የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር በጂቡቲ አርታ ክልል ዛሬ አካሂደዋል።
በመርሃ-ግብሩ ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር አምባሳደር ሐሰን አብዱልቃድር፣ የጂቡቲ የግብርና ሚኒስትር አሕመድ መሐመድ አዋሌህ፣ የጂቡቲ ባህልና ወጣቶች ሚኒስትር ሂቦ ሙሚን አሶዌህ፣ በጂቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ እንዲሁም የኢትዮጵያና የጂቡቲ ወጣቶች ተገኝተዋል።
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ሁለት የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር በጂቡቲ ያካሄደች ሲሆን፤ ዛሬም በአረንጓዴ ዲፕሎማሲ ልዑኳ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ጠንካራ ወዳጅነት ማፅናትን ያለመ የችግኝ ተከላ ለሦስተኛ ጊዜ አካሂዳለች።
ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿና ከመላው አፍሪካ ጋር ያላትን ትብብር በአረንጓዴ ዲፕሎማሲውም ለመድገም እየተንቀሳቀሰች ነው።
ለዚህም ወደ ጂቡቲ ያቀናው የወጣቶች ልዑክ አፍሪካዊ ወንድማማችነትን ለማጠናከር ያለመ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ አካሂዷል።
በችግኝ ተከላው የተገኙት በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር አምባሳደር ሐሰን አብዱልቃድር ኢትዮጵያና ጂቡቲ ዘመን ተሻጋሪ ግንኙነታቸውን ኢትዮጵያ በጀመረችው የአየር ንብረት ለውጥን በጋራ የመቋቋም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብርም እንደሚደግሙት ተናግረዋል።
የጂቡቲ የግብርና ሚኒስትር አሕመድ መሐመድ አዋሌህ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች በጂቡቲ ያካሄዱት የችግኝ ተከላ የኢትዮጵያና የጂቡቲን ጥብቅ ወዳጅነት ወደላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ነው ብለዋል።
የተተከሉ ችግኞችም ኢትዮጵያ ለጂቡቲ የምትሰጠውን ከፍተኛ ሥፍራ የሚያመላክት መሆኑን ጠቅሰዋል።
በጂቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብሩ የሁለቱ ሀገራት የጠበቀ ወዳጅነትን በአረንጓዴ ልማት ከማስተሳሰር ያለፈ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያና የጂቡቲ ወጣቶች እንዳሉት የሁለቱ ሀገራት የወደፊት የጋራ ዕጣ-ፈንታ በወጣቶች የተባበረ ክንድ ብሩህ ይሆናል።
የተካሄደው የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር የሁለቱ ሀገራትን የጠበቀ ወዳጅነትን በአረንጓዴ ልማት የሚያስተሳስር መሆኑን ገልፀዋል።
ወጣቶቹ አክለውም የኢትዮጵያንና የጂቡቲን ወንድማማችነት ተግባራትን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።