ቀጥታ፡

መንግስት በተወሰኑ ምርቶች ላይ የውጭ ምንዛሬ እገዳ መጣሉ እየጨመረ ያለውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት ፋይዳው የጎላ ነው

ጥቅምት 05 ቀን 2015 (ኢዜአ) መንግስት በተወሰኑ ምርቶች ላይ የውጭ ምንዛሬ እገዳ መጣሉ የአገር ውስጥ ምርትን ለማበረታታትና ገንዘቡን ለመሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች በማዋል የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት ፋይዳው የጎላ እንደሆነ የኢኮኖሚክስ መምህሩ ዶክተር ብርሃኑ ደኑ ገለፁ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ  ባንክ በትናንትናው ዕለት በሰጠው መግለጫ 38 ምርቶች ላይ  ላልተወሰነ  ጊዜ የውጭ ምንዛሬ እገዳ መጣሉን አስታውቋል።

ከረሜላ፣ ብስኩቶች፣ ጣፋጭ ነገሮች፣ የፍራፍሬ ጭማቂዎች፣ የታሸጉ ውሃዎች፣ ለስላሳ መጠጦች፣ ሲጋራ፣ የውበት መጠበቂያዎችና ጌጣጌጦች በጊዜያዊነት እገዳ ከተጣለባቸው ምርቶች መካከል ይገኛሉ።     

የተገጣጠሙ የቤት አውቶሞቢልና ባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎች፣ የተገጣጠሙ ሞተር ተሽከርካሪዎች የኤሌክትሪክ ሞተር ሳይክልን ሳይጨምር እገዳ ከተጣለባቸው ምርቶች ውስጥ እንደሚካተቱም መግለጫው ያትታል።

የውጭ ምንዛሬ አቅርቦቱ በዋናነት ለመሰረታዊ የምግብ ሸቀጦች፣ ለመድኃኒት፣ ለሕክምና መሳሪያዎችና ለምርት ግብዓት ለሚውሉ ምርቶች ቅድሚያ ይሰጣል ተብሏል።

መንግስት የወሰደውን ይህን እርምጃ አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር ዶክተር ብርሃኑ ደኑ እንዳሉት የማስተካከያ እርምጃው በተገቢው መልኩ ከተተገበረ ኢኮኖሚን ለማረጋጋት አስተዋፅኦ ይኖረዋል።

አገራት የውጭ ምንዛሬ እጥረትና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መቀዛቀዝ ሲገጥማቸው እና የመዋዕለ ነዋይ ፍሰትና ከውጭ የሚመጣው ገንዘብ በማይመጣጠንበት ጊዜ የማስተካከያ እርምጃ ይወስዳሉ።

የማስተካከያ እርምጃው ማክሮ ኢኮኖሚውን ለማረጋጋትና እድገትን ለማረጋገጥ በሚል የሚወሰድ መሆኑን ተናግረዋል።

የተወሰኑ እቃዎች ላይ የተወሰደው የውጭ ምንዛሬ እገዳ በተለይ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ከውጭ የሚገቡትን ምርቶች በአገር ውስጥ ምርቶች ለመተካት የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል።

ጃፓን፣ ቻይና እንዲሁም የላቲን አሜሪካ አገራት የፋይናንስ ችግርና የኢኮኖሚ ማዕቀብ በተጣለባቸው ወቅት ከውጭ በሚገቡ እቃዎች ምትክ የአገር ውስጥ ምርትን በማሳደግ አሁን ለደረሱበት የኢኮኖሚ ደረጃ መድረሳቸውን አንስተዋል።

አገር ውስጥ ያለው የግል ባለሃብት ከመንግስት ጋር በአጋርነት የአገር ውስጥ ምርትን በጥራትና በስፋት ማምረት ከተቻለ እድገትን የሚያመጣ ብሎም የምርቶችን አቅርቦት እጥረት በመፍታት ዋጋ እንዲረጋጋ ያስችላል ብለዋል።

የውጭ ምንዛሬን እንደ መድኃኒት፣ የምግብ ሸቀጦችና የምርት ግብአቶች ለመሳሰሉ መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች ለማዋል ያስችላልም ነው ያሉት።

የአገር ውስጥ ቁጠባ እንዲያድግና የውጭ ብድር ላይ መመርኮዝንና የእዳ ጫናን ለመቀነስ ፋይዳ ያለው መሆኑንም ተናግረዋል።

ቀደም ሲል መንግስት ዋጋን ለማረጋጋት ምርቶች በፍራንኮ ቫሉታ እንዲገቡ ሲደረግ ቢቆይም አንዳንድ አካላት ግን አግባብ ባልሆነ ሁኔታ ተጠቅመው ዋጋ እንዲንር ማድረጋቸውን አንስተዋል።

የቁጥጥር ስርዓት አስቀድሞ በመዘርጋት በሚፈለገው ልከ ስላልተሰራ ኢኮኖሚው እንዳይረጋጋ ማድረጉን ጠቅሰው አሁንም መሰል ችግር እንዳይከሰት ቁጥጥር በማድረግ ለውጤታማነቱ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

መንግስት የኢኮኖሚው ቁልፍ የሆኑ የገንዘብ ስርጭት፣ አገባብና አወጣጡን የውጭ ምንዛሬና የመሳሰሉት ላይ በሚገባ ቁጥጥር በማድረግ ኢኮኖሚውን መስመር ማስያዝ እንዳለበትም ገልፀዋል።

መንግስት ገበያ ለማረጋጋት በሸማች ህብረት ስራ ማህበራት የሚያቀርባቸው ምርቶች በተገቢው መልኩ እየደረሱ መሆኑንና የውጭ ምንዛሬ ቅድሚያ የተሰጣቸው አካላት በሚገባ ጥቅም ላይ እያዋሉ መሆኑን መከታተል እንዳለበት ጠቁመዋል።

የብሔራዊ ባንክ ማክሮ ኢኮኖሚን ለማረጋጋት ከሚወስዳቸው እርምጃዎች አንዱ የእቃዎችን ዋጋ ማረጋጋት መሆኑን አንስተው ለዚህ ደግሞ የገንዘብን ስርጭትን መቆጣጠር አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የወጣው እገዳ በአግባቡ ስራ ላይ ከዋለና ህዝቡና ባለሙያው ከደገፈው ውጤታማ መሆኑንም ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ የእነዚህ ምርቶች ላልተወሰነ ጊዜ መታገድ ከሚፈጥርበት ስሜት ይልቅ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማረጋጋትና ሉዓላዊነቷን ጠብቃ ለመሄድ የሚያስችል እርምጃ መሆኑን መገንዘብ ይገባዋልም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም