ኮሚሽኑ ለአቅመ ደካሞች ድጋፍ የሚውል ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ኮሚሽኑ ለአቅመ ደካሞች ድጋፍ የሚውል ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ
ሚዛን አማን፣ ጥቅምት 05 ቀን 2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚውል 11 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የሚገመት የምግብ፣ የአልባሳትና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።
የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ሙሉጌታ በየነ ድጋፉን ለክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ አስረክበዋል።
የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ህግ በማስከበር ተግባር በህግ አግባብ የተወረሱ ንብረቶችን ለህዝብ እንደሚያደርስ ምክትል ኮሚሽነር ሙሉጌታ በርክክብ ሥነሥርዓቱ ላይ ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም 43 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው ንብረቶችን ለክልሉ ድጋፍ ማድረጉንም አስታውሰዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ኮሚሽኑ ላደረገው ድጋፍ በክልሉ መንግሥት ስም አመስግነዋል።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም ኮሚሽኑ ያደረገው ድጋፍ በክልሉ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚደርስ ተናግረዋል።