ቀጥታ፡

በሰው ሰራሽ አስተውሎት /አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ/ ዘርፍ የወጣቶችንና ታዳጊዎችን ተሳትፎ ለማጎልበት እየተሰራ ነው-አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት

ጥቅምት 05/2015(ኢዜአ) በሰው ሰራሽ አስተውሎት /አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ/ ዘርፍ የወጣቶችንና ታዳጊዎችን ተሳትፎ ለማጎልበት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በሰው ሰራሽ አስተውሎት /አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ/ ዘርፍ ለሁለት ወራት ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል።          

ተማሪዎቹ በሰው ሰራሽ አስተውሎት /አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ/ ዘርፍ ዝንባሌ ያላቸው ሲሆኑ ሥልጠናቸውን የወሰዱት የክረምት ወራት እረፍታቸውን ተጠቅመው ነው፡፡

በሳይንስ ሙዚየም በተካሄደው የምርቃት ሥነ-ሥርዓት ላይ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ተገኝተዋል።             

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ አሁን ላይ አገራት ሰው ሰራሽ አስተውሎትን የእድገታቸው ቁልፍ እያደረጉት ነው።         

ኢትዮጵያን ከዘርፉ ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ዘርፉ ቅንጦት ሳይሆን ወሳኝ መሆኑን መረዳት ይገባል ብለዋል።       

በተለይም ወጣቶች እና ታዳጊዎች ላይ መሥራት በቀጣይ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ ውጤታማ ተግባር ለማከናወን አጋዥ መሆኑንም አንስተዋል።   

ለዚህም ዝንባሌ ያላቸው ታዳጊዎች አቅማቸውን አሟጠው እንዲጠቀሙ የሚረዱ ሥልጠናዎችንና ድጋፎችን ለመስጠት የሚያግዙ አሰራሮች እየተዘረጉ መሆኑንም አብራርተዋል።  

ተመራቂዎች በመስኩ ክህሎታቸውን የበለጠ በማሳደግ አገር የሚጠቅም ተግባር ላይ መሳተፍ እንደሚገባቸውም አፅንኦት ሰጥተዋል።

የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው፤ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ የሚከናወኑ የፈጠራ ሥራዎች ወደ መሬት እንዲወርዱ ሚኒስቴሩ ኢንስቲትዩቱን ጨምሮ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር ይሰራል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከተመራቂዎቹ ብዙ እንደምትጠብቅ የገለጹት ሚኒስትሯ አገሪቱ በዓለም ተወዳዳሪ እንድትሆንና ስሟ እንዲጠራ አሻራችሁን ማኖር ይጠበቅባችኋል ብለዋል።

ተመራቂ ተማሪዎች በበኩላቸው፤ በሁለት ወራት ቆይታቸው በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ ተሳትፏቸውን የበለጠ ለማሳደግ የሚረዳቸውን ዕውቀት መቅሰማቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም