የጤና ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማቱ ለአገር መከላከያ ሠራዊት ከ112 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አደረጉ

220

ጥቅምት 5/2015(ኢዜአ)   የጤና ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማቱ ለአገር መከላከያ ሠራዊት ከ112 ሚሊዮን ብር በላይ በጥሬ ገንዘብ እና በዓይነት ድጋፍ አደረጉ፡፡

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ድጋፉን ለአገር መከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሉዊጂ አስረክበዋል።

ሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማቱ 110 ሚሊዮን ብር  በጥሬ ገንዘብ እና ከ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የዓይነት ድጋፎችን አድርገዋል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በወቅቱ ባስተላለፉት መልእክት፤ ለኢትዮጵያ ክብርና ሉዓላዊነት  ለሚዋደቀው ለጀግናው የመከላከያ ሠራዊት ሁለንተናዊ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የጤና ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማቱ የህልውና ዘመቻው ከተጀመረ አንስቶ ላለፉት ሁለት ዓመታት የሕክምና ድጋፍ በመስጠት እና በጦርነቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ በማድረግ ሀገራዊ ግዴታቸውን ሲወጡ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡

አሸባሪው ህወሃት በኢትዮጵያ ላይ ሦስተኛውን ዙር ጦርነት ከከፈተ በኋላም ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ ከ118 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የመድኃኒት ሥርጭት መደረጉን ገልጸዋል፡፡

የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሉዊጂ በበኩላቸው፤ በዛሬው እለት የጤና ሚኒስትር እና ተጠሪ ተቋማቱ ላደረጉት ድጋፍ አመስግነው፤ በቀጣይም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም