ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከዓለምአቀፉ የቀይመስቀል ኮሚቴ ምክትል ፕሬዚዳንት ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከዓለምአቀፉ የቀይመስቀል ኮሚቴ ምክትል ፕሬዚዳንት ጋር ተወያዩ
ጥቅምት 05 ቀን 2015 (ኢዜአ) በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ከሚገኘው 10ኛው የጣና ፎረም ጉባዔ ጎን ለጎን የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከዓለምአቀፉ የቀይመስቀል ኮሚቴ ምክትል ፕሬዚዳንት ጂሌስ ካርቦኔር ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱ አቶ ደመቀ የዓለምአቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ በኢትዮጵያ እያደረጋቸው ላለው የሰብአዊ አገልግሎት ምስጋና አቅርበዋል።
በተለይ በአሁኑ ወቅት በሰሜን ኢትዮጵያ ባለው ግጭት ተጎጂ ለሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ቀይ መስቀል እያደረገ ያለውን ሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
ሰላምን በዘላቂነት ለማስፈን የኢትዮጵያ መንግስት ኮሚሽን በማቋቋም ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ አቶ ደመቀ በውይይቱ ላይ አስታውቀዋል።
የዓለምአቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ምክትል ኘሬዚዳንት ጂሌስ ካርቦኔር በበኩላቸው ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር መስራት እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
በውይይቱ ላይ ባለፈው አመት ቀይ መስቀል በሰሜን ኢትዮጵያ 63 ያህል በረራዎችን በማድረግ ሰብአዊ እርዳታን ለተጎጂ ማህበረሰብ ማድረሱን አስታውሰዋል።
በኢትዮጵያ ሰላምን ለማረጋገጥ የሚካሄደው የሰላም አማራጭ ውጤታማ እንዲሆን አለምአቀፉ የቀይመስቀል ማህበር የበኩሉን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ምክትል ኘሬዚዳንቱ ገልፀዋል።
አቶ ደመቀ መኮንን በተጨማሪም ከሱዳኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሊ ኤልሳዲግ አሊ ጋርም በሁለትዮሽ እና ቀጠናዊ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ በባህር ዳር ውይይት ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ጠቁሟል።