በኢትዮጵያ ሰላምና ጸጥታን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ሕግ አውጭዎች በተጠናከረ መልኩ ኃላፊነታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል - አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ሰላምና ጸጥታን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ሕግ አውጭዎች በተጠናከረ መልኩ ኃላፊነታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል - አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ
ጥቅምት 5 2015 (ኢዜአ) “በኢትዮጵያ ሰላምና ጸጥታን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ሕግ አውጭዎች በተጠናከረ መልኩ ኃላፊነታቸውን መወጣት ይገባቸዋል” ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።
አገር አቀፍ፣የክልሎችና የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ሕግ አውጭዎች የምክክር መድረክ በጅማ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
ጉባኤው ምክር ቤቶች በአገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚመክሩበትና ልምድ የሚለዋወጡበት መሆኑ ተገልጿል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ አገራዊ ምክክር በማድረግ ሰላምን ዕውን ማድረግ የዓመቱ ትኩረት ነው፤ምክር ቤቶችም በዚህ ረገድ ትልቅ ሚና አላቸው ብለዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት የኢትዮጵያን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ሰፊ ስራዎች እንደሚጠብቁና ሕግ አውጭዎች ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው አመልክተዋል።
የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ሰዓዳ አብዱራህማን በበኩላቸው መድረኩ አገርን ወደፊት ለማራመድ በሚደረገው ጥረት ሕግ አውጪዎች ተሞክሮ እንዲለዋወጡ የሚያግዝ እንደሆነ ተናግረዋል።
በጋራ መድረኩ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ስራ ሂደት በኮሚሽነሮቹ ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግበት ተገልጿል።
የክልል ምክር ቤቶች ተሞክሮዋቸውን የሚያቀርቡ ሲሆን በፌዴሬሽን ምክር ቤት በኩል ደግሞ በመንግሥታት ግንኙነት ላይም ምክክር እንደሚካሄድ ተነግሯል።