ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ና የባለብዙ ወገን ትብብር ለማጠናከር እየሰራች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ና የባለብዙ ወገን ትብብር ለማጠናከር እየሰራች ነው
ጥቅምት 5 /2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያና የቻይና በባለብዙ ወገን የትብብር መስኮችን ይበልጥ ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ።
በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የኢትዮጵያና የቻይና ግንኙነት ከ50 በላይ ዓመታት ከመዝለቁም ባለፈ የትብብር መስኩ አድማሱን እያሰፋ መጥቷል ብለዋል።
በተለይም ቻይና በኢትዮጵያ በበርካታ የልማት መስኮች ላይ ንቁ ተሳታፊ የሆነች ወዳጅ አገር መሆኗን ጠቅሰው ቻይና የኢትዮጵያን የልማት እንቅስቃሴዎች በፋይናንስና በቴክኒክ ድጋፍ እያገዘች መሆኗን ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት በመንገድ መሰረት ልማት፣ በሃይል ልማት፣ በትራንፖርትና የኢትዮጵያ መንግሥት ትኩረት በሰጣቸው በሌሎች ድህነት ቅነሳ የልማት ሴክተሮች ላይ ድጋፍ ማድረጓን ጠቅሰዋል።
ጎን ለጎንም የቻይና ባለኃብቶች በኢትዮጵያ በማኑፋከቸሪንግ በተለይም ደግሞ በጨርቃ ጨርቅና በፋርማሲዩቲካል ዘርፎች ላይ ተሳትፏቸው እየጎለበተ መምጣቱን ነው ያብራሩት።
የቻይና ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ያላቸውን ተሳትፎ የበለጠ ለማጠናከር ኤምባሲው በኢትዮጵያ ያለውን የኢንቨስትመንት አማራጭ አገሪቱ ከያዘችው የአስር ዓመት መሪ እቅድ ጋር በማሰናሰል የማስተዋወቅ ሥራ በስፋት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች በቻይና የገበያ እድል እንዲያገኙ ለማድረግ በሚደረገው ጥረትም፤ የኢትዮጵያ ቡናና ሰሊጥ በቻይና ገበያ ትልቅ ድርሻ እየያዙ መሆኑን ጠቁመው ሌሎችም ምርቶች እንዲሁ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም የአትክልት ና የሥጋ ምርቶች የቻይና ገበያን እንዲቀላቀሉ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸው በኢትዮጵያ በኩል ምርቶቹ ላይ እሴት መጨመር ከተቻለ ከፍተኛ ጥቅም ማግኘት ይቻላል ነው ያሉት።
ቻይና የደረሰችበትን የእድገት ተሞክሮ ለመቀመር የሚያስችል በቴክኖሎጂና በሳይንስ ዘርፍ የልምድ ልውውጡን ለማጠናከር የሚያስችሉ የትምርትና የሥልጠና ድጋፎችም እየተጠናከሩ መሆኑን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ አሁን በሰሜኑ የአገሪቱ አከባቢ ከገጠማት ጦርነት ጋር በተያያዘ ጉዳዩ የውስጥ ጉዳይ እንደሆነና ኢትዮጵያ እራሷ መፍታት እንዳለባት ቻይና በመርህ ላይ የተመረኮዘ አቋም ስታንጸባርቅ መቆየቷን ገልጸዋል።
ያም ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ የገጠማት ችግር የአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት በሚካሄደው የሠላም ጥረት መፈታት አለበት የሚል አቋሟን ያለምንም መዘናፍ መግለጿንም ነው የገለጹት።
በተጓዳኝም ኢትዮጵያ በምሰራቅ አፍሪካ ሰላምና መረጋጋት በማስፈን ያላትን አብርክቶ ከግምት በማስገባት በአከባቢውም ሆነ በመላው አፍሪካ ሰላም ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ከቻይና ጋር በቅርበት መሥራቷን ትቀጥላለች ብለዋል።