የኢትዮጵያ አርብቶ አደሮች ልማት ፎረም በይፋ ተመሠረተ

25

ጥቅምት 4/2015(ኢዜአ) የእንስሳት ሀብት ልማትና ግብይት ችግሮችን ለመፍታት ያስችላል የተባለው የኢትዮጵያ አርብቶ አደሮች ፎረም በይፋ ተመሠረተ።

በኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን አስተባባሪነት የተመሰረተው ፎረሙ በአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች የሚታየውን የእንስሳት ሃብት ልማትና ግብይት ችግር ይፈታል ተብሏል።

የግብርና ሚኒስቴር፣ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን በበላይነት የሚመሩት መሆኑም ተገልጿል።   

የግብርና ሚኒስትሩ ዑመር ሁሴን፤ በአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች በእንስሳት ሀብት ልማት ዙሪያ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ቅንጅታዊ ስራን ይጠይቃል ብለዋል።

በአገሪቱ ያለው የግብርና ዘርፍ ከፍተኛ መነቃቃት ቢያሳይም ለእንስሳት ሀብት የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆኑንም በመሠረታዊ ችግርነት አንስተውታል።

የእንስሳት ሀብት ልማትን በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል በአሥር ዓመቱ የግብርና መሪ ዕቅድ ውስጥ አካቶ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ በበኩላቸው ፎረሙ በአርብቶ አደሮች የኑሮ ዘይቤና ባህላዊ ማንነት ላይ መሰረት አድርጎ መመስረቱ የላቀ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።

የአርብቶ አደሩን የእንስሳት ሀብት ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ መጠቀም ከተቻለ በሀገር ደረጃ ምርታማነትን ማሳካት እንደሚቻልም አመልክተዋል።

የሀገሪቱን 60 ከመቶ የያዘው አርብቶ አደርና ከፊል አርብቶአደር ሰፊ መሬት፣ ውሃ፣ የእንስሳትና የተፈጥሮ ሀብት ያለው በመሆኑ ፎረሙ አስፈላጊውን ፋይናንስ በማሰባሰብ በጠንካራ አደረጃጀት ላይ ተመስርቶ እንዲንቀሳቀስ ይደረጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፍሬዓለም ሽባባው፤ በአርብቶ አደር አካባቢ የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች በተደጋጋሚ የሚጠቁ በመሆናቸው ችግራቸውን ለመቅረፍ ሁሉም ሊተባበር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

እነሱን መደገፍ ማለት አገሪቱን ወደ ተሻለ ኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ማድረስ መሆኑንም አመልክተዋል።

ፎረሙን ዘመናዊ የእንስሳት እርባታ፣ ጠንካራ የገበያ ትስስርና የእንስሳት ጤና አገልግሎትን እንደሚያጠናክር ጠቁመዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ሕገወጥ የቁም እንስሳት ንግድና ኮንትሮባንድን ለመግታት ያግዛል ብለዋል፡፡

በሀገሪቱ የአፋር፣ የሶማሌ፣ የኦሮሚያ፣ የደቡብ ምዕራብ፣ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ ጋምቤላና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎችን የሚያካትት 220 ወረዳዎች የአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም