የመገናኛ ብዙሃን የአገር ግንባታና ህብረ-ብሔራዊ አንድነት ላይ በልዩ ትኩረት ሊሰሩ ይገባል- አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር - ኢዜአ አማርኛ
የመገናኛ ብዙሃን የአገር ግንባታና ህብረ-ብሔራዊ አንድነት ላይ በልዩ ትኩረት ሊሰሩ ይገባል- አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር
ጥቅምት 4/2015(ኢዜአ) የመገናኛ ብዙሃን የአገር ግንባታና ህብረ-ብሔራዊ አንድነት ላይ በልዩ ትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘው ተሻገር ተናገሩ።
ለ17ኛ ጊዜ የሚከበረው የዘንድሮው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን "ሕብረ-ብሔራዊ አንድነት ለዘላቂ ሰላም" በሚል መሪ ሃሳብ ህዳር 29 ቀን በሀዋሳ ከተማ ይከበራል።
የፌዴሬሸን ምክር ቤት የበዓሉን አከባበርና አጠቃላይ ዝግጅት በማስመልከት ከመገናኛ ብዙሃን አመራሮች እና ከክልል የኮሚንኬሽን ቢሮ ሃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፤ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በየዓመቱ መከበሩ ብዝሃነትን ለማስተናገድና አገራዊ አንድነትን ለማረጋገጥ ከፍ ያለ ፋይዳ አለው ብለዋል።
የዘንድሮውም በዓል በፌደሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነት በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አስተናጋጅነት በሀዋሳ የሚከበር መሆኑን ተናግረዋል።
"ከሚለያዩን ነገሮች ይልቅ አንድ የሚያደርጉን በርካታ መገለጫዎች አሉ ያሉት አፈ ጉባኤው የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን የአገር ግንባታና ህብረ-ብሔራዊ አንድነት ላይ በልዩ ትኩረት እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
የፌደሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ዛህራ ሁመድ፤ መገናኛ ብዙሀን የህዝቡን አንድነትና ህብረት የሚያጠናክሩ ስራዎችን መስራት ላይ ሊያተኩሩ ይገባል ብለዋል።
በአሉ በተለያዩ ሁነቶች እንደሚከበር ገልጸው የሀገር ሉአላዊነት እንዳይደፈርና አገር ወዳድነታቸውን በተግባር ያስመሰከሩ አካላትን በማመስገንና እውቅና በመስጠት እንደሚከበርም አክለዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የጋራ አጀንዳ የሚያመጡ ጉዳዮች ላይ በማተኮር መገናኛ ብዙሃን ለአገር ልማትና ግንባታ እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
በአሉ ለአንድ ቀን ተከብሮ የሚተው ብቻ ሳይሆን የህዝቦችን አንድነትና አብሮነት ለማጠናከር የዘወትር ስራ ሊሆን ይገባልም ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በዓል ህገ-መንግስታዊ እኩልነትና ኅበረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያሳይ መልኩ በየዓመቱ ህዳር 29 ቀን የሚከበር መሆኑ ይታወቃል።
16ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ‹‹ወንድማማችነት ለህብረ ብሄራዊ አንድነት›› በሚል መሪ ሃሳብ በድሬዳዋ ከተማ መከበሩ ይታወሳል።