በአዲስ አበባ የሚገኘው የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መሰብሰቢያ አዳራሽ እድሳት ሊደረግለት ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ የሚገኘው የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መሰብሰቢያ አዳራሽ እድሳት ሊደረግለት ነው
ጥቅምት 4 ቀን 2015 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ቅጥር ግቢ ሚገኘው የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መሰብሰቢያ አዳራሽ ህንፃ በ57 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር እድሳት ሊደረግለት መሆኑ ተገለጸ።
ህንፃው እ.አ.አ በ1961 ለመንግስታቱ ድርጅት መሰብሰቢያ እንዲውል ታስቦ የተሰራ ሲሆን በህንፃው የሚገኘው መሰብሰቢያ አዳራሽም በርካታ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን አስተናግዷል።
የቀድሞው የኢትዮጵያ መሪ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴን ጨምሮ ሌሎች የአህጉሪቷ መሪዎች እ.አ.አ. በ1963 በዚሁ አዳራሽ በመሰባሰብ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን መስርተዋል።
መሪዎቹ የአፍሪካዊያንን ሃሳብ ለአለም እንዲደርስ ያስቻሉ በርካታ ታላላቅ የውሳኔ ሃሳቦችን ያሳለፉበት መሆኑንም ታሪክ የማይዘነጋው ነው።
በርካታ ዓመታትን የተሻገረ እድሜ ያስቆጠረው ህንጻና በውስጡ የሚገኙ አዳራሾች በ57 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር እድሳት ከተደረገላቸው በኋላ የአፍሪካዊን ቅርሶች የሚታዩበት ሙዚየም እንደሚሆኑ ተገልጿል።
ህንፃው ታሪካዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ እድሳት እንደሚደረግለት የተገለጸ ሲሆን የእድሳት ወጪውም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደሚሸፈን ተነግሯል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ፤ የአፍሪካውያን ኩራት የሆነው ታሪካዊ ህንፃ በዘመናዊ መልኩ እድሳት ተደርጎለት የአፍሪካዊያን ቅርሶች እንደሚታዩበት አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት የህንፃ እድሳቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ አስፈላጊ የሆኑ ድጋፎችን እንደሚደርግም አረጋግጠዋል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ምክትል ሥራ አስፈፃሚ አንቶኒዮ ፔድሮ፤ አፍሪካ ለቀሪው ዓለም የቱሪስት መዳረሻ የሚውሉ ታሪካዊ ቅርስና ሃውልቶች ባለቤት መሆኗን ገልጸዋል።
የህንፃ እድሳቱ ሲጠናቀቅም የአፍሪካዊያንን ቅርሶች ለቱሪዝም ኢንደስትሪው በማቅረብ የአህጉሪቷን ብዝሃ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለማሳደግ መታቀዱን ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ የዘመናዊት አፍሪካን ቅርሶች ለእይታ ከማቅረብ በተጨማሪ የኢትዮጵያን የቱሪዝም እንቅስቃሴ በመደገፍ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።
የአዳራሹ የእድሳት ፕሮጀክት ኃላፊ አንቶኒዮ ባዮ፤ እድሳቱ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በታገዘና ታላላቅ ሁነቶች ማስተናገዱን በሚገልጽ መልኩ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እንሰራለን ብለዋል።
የህንፃ እድሳቱ ከተጠናቀቀ በኋላ የአፍሪካዊያንን ታሪካዊ ቅርሶች በመያዝ ለጎብኝዎች ክፍት የሚደረግ ሲሆን የመዲናዋን የቱሪስት ፍሰት በማሳደግ ተጨማሪ ሚና እንደሚኖረው ይጠበቃል።