ቀጥታ፡

"ኢትዮጵያ የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ተምሳሌት ናት"--የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ

ባህር ዳር (ኢዜአ) ጥቅምት 4/2015 "ኢትዮጵያ የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ተምሳሌት ናት" ሲሉ የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ።

"የደህንነት ስጋቶችን መቀነስ፣ ችግሮችን መቋቋም የምትችልና የምንመኛትን አፍሪካ መገንባት" በሚል መሪ ቃል የጣና ፎረም የቅድመ ፓናል ውይይት ዛሬ በባህር ዳር ከተማ መካሄድ ጀምሯል።

አቶ ሃይለማርያም በውይይቱ ላይ እንደተናገሩት፣ አሁን ያለውም ሆነ በየጊዜው የነበሩት  የኢትዮጵያ መንግስታት ለአፍሪካ ህዝቦች ነጻነት ጽኑ አቋም አላቸው።

በየመንግስታቱ የተስተዋለው መላ አፍሪካውያን ከቅኝ አገዛዝ ነጻ እንዲወጡ የማገዙ ሥራ እስካሁን ድረስ ተጠናክሮ የቀጠለ መሆኑንም ነው አቶ ሃይለማርያም ያመለከቱት።

በዚህም ኢትዮጵያ ሌሎች የአፍሪካ የነፃነት አርበኞችን በማስተባበር ለፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ ተምሳሌት መሆኗን በትግባር ጭምር ያስመሰከረች ሃገር ናት ሲሉ ገልፀዋል።

የፎረሙ አወያይ ፕሮፌሰር ፓትሪክ ሉሙምባ በበኩላቸው "የዛንቢያው ኬኔት ካውንዳ፣ የጋናው ክዋሜ ንኩርማህ፣ የታንዛኒያው ጁሌስ ኔረሬና ሌሎች የአፍሪካ መሪዎች ለአህጉሪቱ ነጻነት የሰሩ ናቸው" ብለዋል።

የአሁኑ ትውልድም እነዚህን መሪዎች ፈለግ በመከተል ለፓን አፍሪካኒዝም ተጠናክሮ መቀጠል የማይተካ ሚና መጫወት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የአፍሪካን ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ትስስርን መፍጠርና ከውጭ ተጽዕኖ የተላቀቀ ፖለቲካል አስተሳሰብ መገንባት እንደሚገባም ፕሮፌሰር ፓትሪክ ገልጸዋል።

ለዚህም እንደ ጣና ፎረም ባሉ መድረኮች ችግር ፈቺ የሆኑ ሃሳቦችን በማመንጨትና የሚቀርቡ ሀሳቦችን በግብአትነት መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን ነው ያስገነዘቡት።  

በፎረሙ የቅድመ ፓናል ውይይት ላይ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የመጡ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም