በኢትዮጵያ የሚስተዋለውን የውጭ ምንዛሬ ችግር ለመፍታት የውጭ ምንዛሬ አስተዳደርን መፈተሽና ተጠያቂነትን ማስፈን ይገባል- የምጣኔ ሃብት ምሁር - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የሚስተዋለውን የውጭ ምንዛሬ ችግር ለመፍታት የውጭ ምንዛሬ አስተዳደርን መፈተሽና ተጠያቂነትን ማስፈን ይገባል- የምጣኔ ሃብት ምሁር
ጥቅምት 4/2015/ኢዜአ/ በኢትዮጵያ የሚስተዋለውን የውጭ ምንዛሬ ችግር ለመፍታት የውጭ ምንዛሬ አስተዳደርን በመፈተሽ ተጠያቂነትን ማስፈን እንደሚገባ የምጣኔ ሃብት ምሁር ገለጹ።
በአገሪቱ የሚስተዋለው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለበርካታ የልማት ክንውኖች፣ንግድና ግብይት ከፍተኛ ችግር ሲሆን ይስተዋላል።
የተለያዩ ተቋማት በሙሉ አቅማቸው እቅዳቸውን ለመፈጸም የሚቸገሩበት አንደኛው ምክንያትም የውጭ ምንዛሬ እጥረት መሆኑ ይነገራል።
በመሆኑም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ለዘፈቀደ አሰራሮች የተጋለጠውን የውጭ ምንዛሬ አጠቃቀም መንግስት ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ማስተካከል አለበት ይላሉ ምሁራን።
በጉዳዩ ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የምጣኔ ሀብት ምሁሩ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ፤ በፍራንኮቫሎታ ምርቶችን እንዲያስገቡ የተፈቀደላቸው አካላት ለህገ-ወጥ አሰራር አለመጋለጣቸውን መፈተሽ የሚገባ መሆኑን ገልጸዋል።
የተፈቀደላቸውን የውጭ ምንዛሬ ለታለመለት ዓላማ ካላዋሉ ችግሩን የማባባስ እድላቸው ሰፊ በመሆኑ መንግስት ቁጥጥሩን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በውጭ ምንዛሬ ላይ የሚታየው ህገ-ወጥ አሰራር የአገርን ህልውና የሚፈታተን በመሆኑ መንግስት የውጭ ምንዛሬ አስተዳደርን መፈተሽ እንዲሁም ተጠያቂነትን የማስፈን ስራ መስራት አለበት ብለዋል።
የገቢ እና የወጪ ንግድ ሚዛንን ማስተካከል ደግሞ በውጭ ምንዛሬ ላይ የሚታየውን ችግር ለመፍታት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
ለሚታየው የውጭ ምንዛሬ እጥረት አገሪቱ ወደ ውጭ የምትልካቸውን ምርቶች ብዛትና ጥራት ማሳደግ እንዲሁም ከውጭ የምታስገባውን የምርት መጠን መቀነስም መፍትሄ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
የገንዘብ ፖሊሲውን በአግባቡ ተግባራዊ በማድረግ ህገ-ወጥ ገንዘብ በገበያው ላይ እንዳይገባ መንግስት ተገቢውን ቁጥጥር ሊያደረግ ይገባዋልም ነው ያሉት።
የውጭ ምንዛሬ በህጋዊ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ እየተወሰዱ ያሉ የማበረታቻ ስርዓቶችን ማጠናከርም እንደሚገባ ይመክራሉ።
በውጭ ምንዛሬ ላይ የሚታየውን ችግር ለመፍታት የፋይናንስ ስርዓቱን ከማሻሻል ባሻገር በዘርፉ ጤናማ የውድድር መንፈስ እንዲፈጠር ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይገባልም ነው ያሉት።
ለዚህ ደግሞ ከፋይናንስ ዘርፉ ተዋናዮች፣ ባለድርሻ አካላትና የዘርፉ ሀሳብ አመንጪዎችን ያሳተፈ ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በውጭ ምንዛሬ ህገ-ወጥ እንቅስቃሴ ላይ ተሳትፎ ያላቸውን ህገ ወጦች በመለየት የባንክ አካውንታቸውን እንዳይንቀሳቀስ ማድረጉ ይታወሳል፡፡