ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፈረንሳይ የአቪየሽን ኩባንያዎች ጋር ትብብሩን ለማጠናከር ዝግጁ ነው

ጥቅምት 3/2015 (ኢዜአ)  የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአቪየሽን ዘርፍ ከተሰማሩ የፈረንሳይ ኩባንያዎች ጋር ያለውን ትብብር ለማጠናከር ዝግጁ መሆኑን የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ገለጹ።

በፈረንሳይ ኤምባሲ አዘጋጅነት የኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ  ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩበት 125ኛ ዓመት በተለያዩ ሁነቶች እየተከበረ ይገኛል።

በዛሬው እለትም በአቪየሽን ዘርፍ የተሰማሩ የፈረንሳይ ኩባንያዎች ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የስራ ኃላፊዎች ጋር በዘርፉ ለመስራት የሚያስችል ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱ በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው እና በዘርፉ የተሰማሩ ኩባንያዎች የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በዚሁ ወቅት፤ ፈረንሳይ በአቪየሽን ዘርፍ ትልቅ ስም እንዳላት ጠቅሰዋል።

በአቪየሽን ዘርፍ የተሰማሩ የፈረንሳይ ኩባንያዎች የሚያቀርቧቸውን ምርትና አገልግሎቶች ለማስተዋወቅ ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸውን ጠቁመው፤ በትብብር መስራታቸውን የሚያጠናክር ውይይት መደረጉን ነው የተናገሩት።

በሁለቱ ሀገራት መካከል ካለው የኢኮኖሚ ግንኙነት ውስጥ የአቪየሽን ዘርፉ ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድም አቶ መስፍን ተናግረዋል።

በዛሬው እለት ከተወያዩት ኩባንያዎች ውስጥም ግማሽ ያህሉ አሁንም ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በቀጣይም ከሌሎች አዳዲስ ኩባንያዎች ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጅት ማድረጉን ነው የገለጹት።

በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ የፈረንሳይ እና ኢትዮጵያ ግንኙነት ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

ዘንድሮ ሀገራቱ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩበት 125ኛ ዓመት እየተከበረ መሆኑን ገልጸው የዛሬው ሁነትም የዚሁ አካል መሆኑን ጠቅሰዋል።

ዛሬ በተካሄደው ኩነት 16 የፈረንሳይ የአቪየሽን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በዘርፉ ላይ በትብብር ለመስራት የሚችልበት መግባባት መፈጠሩን ገልጸው፤ በቀጣይ ኩባንያዎቹ እና አየር መንገዱ ፍሬያማ ውይይት አድርገው ወደ ተግባራዊ ትብብር እንደሚገቡ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ኢትዮጵያና ፈረንሳይ ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን በፈረንጆቹ 1897 በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ምኒልክ እና በወቅቱ የፈረንሳይ ወኪል ቤሎንስ ላጋርድ በተፈረመ የወዳጅነት ስምምነት መጀመራቸውን የታሪክ መረጃዎች ያሳያሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም