ቀጥታ፡

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በመድኃኒት አምራችነት መሰማራት እንፈልጋለን-የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች

ጥቅምት 3/2015/ኢዜአ/  በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በመድኃኒት አምራችነት መሰማራት እንፈልጋለን ሲሉ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ገለጹ።

በፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ በአስመጪነትና በሌሎች ዘርፎች የተሰማሩ ባለሃብቶች በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ጉብኝት አድርገዋል።

በጉብኝቱ ላይ የተሳተፉ ባለሃብቶች ከውጭና ሌሎች የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ጋር በመተባበር በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ በመድኃኒት አምራችነት የመሳተፍ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መድኃኒትና ሕክምና መገልገያዎች፣ አስመጪዎች እና አከፋፋዮች ዋና ሥራ አስኪያጅ ለማ ገብረየስ፤ በኢንድስትሪ ፓርኮቹ ውስጥ ያሉት ድርጅቶች ወደ ማምረት ተግባር ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሥራ አስኪያጅ መንግስቱ ረጋሳ፤ በፓርኩ 17 ባለሃብቶች ለማልማት በተለያየ ደረጃ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑንም ተናግረዋል።

ድርጅቶቹም በማምረት ላይ፣ በግምባታ ላይ እና በጥናት ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰው፤ በፓርኩ ሁሉም መሰረተ-ልማት የተሟላ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የማርኬቲንግና ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ሄኖክ አሥራት በበኩላቸው፤ ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች በፓርኮቹ ውስጥ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ጠቅሰው የውጭ ምንዛሬን ከማስቀረት ባለፈ የአገር ውስጥ አቅም ለመፍጠር የሚያግዙ ሥራዎች መሰራታቸውን ጠቁመዋል።

ከምቹ ሁኔታዎቹም መካከል የታክስ ክፍያ እፎይታ፣ ከውጭ ለሚያስገቧቸው ግብዓቶች ድጋፍ፣ የውርስ ዋስትና መስጠትና ሌሎችም ድጋፎች መኖራቸውንም ገልጸዋል።

በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች መሰረተ-ልማት በተሟላላቸው 13 ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ 125 ባለሃብቶች ወደ ሥራ የገቡ ሲሆን በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም ከ932 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ እንደተገኘ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም