የኢትዮጵያ የሽምግልና፣ የእርቅና ይቅርታ እሴቶች ለአገራዊ ምክክሩ ጠቃሚ ግብአት እንዲሆኑ የድርሻችንን እናበረክታለን- የአገር ሽማግሌዎች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የሽምግልና፣ የእርቅና ይቅርታ እሴቶች ለአገራዊ ምክክሩ ጠቃሚ ግብአት እንዲሆኑ የድርሻችንን እናበረክታለን- የአገር ሽማግሌዎች
ጥቅምት 3/2015 ዓ.ም /ኢዜአ/ የኢትዮጵያ የሽምግልናና ይቅርታ እሴቶች ለአገራዊ ምክክሩ ግብአት እንዲሆኑ የድርሻቸውን አንደሚያበረክቱ የአገር ሽማግሌዎች ተናገሩ።
ኢትዮጵያ በርካታና የካበቱ ባህላዊ የእርቅ፤የመከባበርና የመነጋገር እሴቶች፤ የመረዳዳት ልምዶች ያሉባት አገር ነች።
እነዚህ እሴቶች ደግሞ በብዙ መልኩ የአገር ሃብትና የሰላም መድህን መሆናቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የጋምቤላ ክልል የአገር ሽማግሌ አቶ ቡል ኬር ፤ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአገር ሽማግሌ አቶ አደም አረደላና የአፋር ክልል የአገር ሽማግሌ ሃጂ ጎዳይ ረሲል ይናገራሉ።
በመሆኑም ለኢትዮጵያ ችግሮች የመፍትሄው ባለቤቶች እኛው በመሆናችን እሴቶቻችንን ተጠቅመን ሰላምና መረጋጋት፣ ንግግርና እርቅ ልንፈጥር ይገባል ብለዋል።
ለዚህ ደግሞ የሽምግልና፣ የእርቅና የይቅርታ እሴቶቻችንን በመጠቀም ለአገራዊ ምክክሩ ግብአት እንዲሆኑ የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል።
በየትኛውም የአገሪቷ አካባቢዎች የምንገኝ የአገር ሽማግሌዎች “ቂምን በይቅርታ ወደ እርቅ ማምጣትና ጥፋትን በማረም ወደ ሰላም የማሸጋገር ትልቅ ሃላፊነት አለብን" ነው ያሉት።
በዚህም የኢትዮጵያ የሽምግልና፣የእርቅና ይቅርታ እሴቶች ለአገራዊ ምክክሩ ጠቃሚ ግብአት እንዲሆኑ የድርሻችንን ለማበርከት ተዘጋጅተናል ሲሉ የአገር ሽማግሌዎቹ አረጋግጠዋል።
የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አረአያ፤ ለምክክሩ ስኬታማነት ባህላዊ የውይይት፣ የሽምግልና እሴቶችን መጠቀም ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የበርካታ እሴቶች ባለቤት መሆኗን ጠቅሰው አገራዊ ችግሮችን በራሳችን የጋራ ጥረትና እሴቶቻቸን መፍታት እንችላለን ሲሉ አረጋግጠዋል።
የአገራዊ ምክክሩ ሂደት ሁሉን አቀፍና አሳታፊ በመሆኑ በዚሁ አውድ የሚከናወን በመሆኑ የሁሉም ትብብር፣ ድጋፍና ተሳትፎ በእጅጉ ያስፈልጋል ብለዋል።
የአገራዊ ምክክሩ ሂደት ቀጣይ ምእራፍ ክንውኖች በመጪው ህዳር ወር ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል።