አሸባሪው ህወሓት በሥልጣን ዘመኑ በአፋኝ ሕግ የሲቪክ ማህበራትን በብዙ መልኩ ገድቧቸው ኖሯል- የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው ህወሓት በሥልጣን ዘመኑ በአፋኝ ሕግ የሲቪክ ማህበራትን በብዙ መልኩ ገድቧቸው ኖሯል- የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት
ጥቅምት 3/2015/ኢዜአ/ አሸባሪው ህወሓት በሥልጣን ላይ በነበረባቸው ዓመታት በአፋኝ ሕግ የሲቪክ ማህበራት እንዳይጠናከሩና ሚናቸውን እንዳይወጡ ማድረጉን የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት ለኢትዮጵያ ምክትል ፕሬዝዳንት ተናገሩ።
ከሥልጣን ከተወገደ በኋላም በፀረ- ሕዝብ ተግባሩ የቀጠለ በመሆኑ ለሰብአዊ መብት ቆመናል የሚሉ ሁሉ በዓለም አቀፉ ሕግ ተጠያቂ ሊያደርጉት ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት ለኢትዮጵያ ምክትል ፕሬዝዳንት ታደለ ደርሰህ፤ አሸባሪው ህወሓት ከምስረታው እስካሁን በሰብአዊነት ላይ እየፈጸመ ያለውን ተግባር በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
አሸባሪው ህወሓት በሥልጣን ላይ በነበረባቸው ዓመታት ለሰው ልጆች የሚሰሩ የሲቪል ማህበራት የተቋቋሙበትን ሚና እንዳይወጡ በአሳሪ ሕጎች አፍኗቸው መቆየቱን ይናገራሉ።
በ27 ዓመታት የሥልጣን ዘመኑ አገርና ሕዝብ ሳይሆን እራሱንና ደጋፊዎቹን ብቻ በመጥቀም አገር ሲገዛ የኖረ ቡድን መሆኑንም ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ምህዳሩን በመዝጋትና የሲቪል ማህበራት ለሀገር የሚገባቸውን ሚና እንዳይወጡ በአፋኝ ሕጎች አስሮ የኖረ መሆኑን አቶ ታደለ ያስረዳሉ።
በሕዝብ ኃይል ከሥልጣን ከተወገደ በኋላም "እኔ የማልመራት አገር ትፍረስ" ብሎ በመነሳት በሽብር ተግባር ላይ ተሰልፎ በአገርና ሕዝብ ላይ ግፍና በደል መፈፀሙን ቀጥሎበታል ነው ያሉት።
የአሸባሪ ቡድኑ ከስልጣን መወገድ በተለይም የሲቪል ማህበራት ሕግ በመሻሻሉ እራሳቸውን አጠናክረው የተቋቋሙለትን ዓላማ መፈፀም እንዲችሉ መልካም አጋጣሚ ተፈጥሯል ብለዋል።
የሲቪል ማህበራት የመደራጀት፣ የመንቀሳቀስ፣ ንብረት የማፍራትና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት በአግባቡ በመተግበር ላይ በመሆኑ ጥሩ አጋጣሚ ሆኗል ነው ያሉት።
በዚህም ማህበራቱ ከመንግሥት ጋር በመቀናጀት ሀገራዊ ሚናቸውን በአግባቡ በመወጣት ላይ መሆናቸውን ምክትል ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
አሸባሪ ቡድኑ አሁንም በሚያገኛቸው አጋጣሚዎች በፀረ-ሕዝብ ተግባሩ የቀጠለ መሆኑን ገልጸው፤ በተለይም ለሰብአዊ መብት ቆመናል የሚሉ ሁሉ በሕግ ተጠያቂ ሊያደርጉት ይገባል ብለዋል።
ከአንዳንድ ምዕራባዊያን አገራት የተራድኦ ድርጅቶችና ሌሎች የውጭ አካላት ጋር የጥቅም ትስስር በመፍጠር አሁንም በለመደው ተግባር ቀጥሎበታል ነው ያሉት።
የሽብር ቡድኑ ህፃናትን ለጦርነት እያሰለፈ፣ ሰብአዊ ድጋፍን በዘረፋም ይሁን በተለያዩ መንገዶች ለራሱ ጥቅም እያዋለ በዝምታ ሳይሆን መታለፍ ያለበት በዓለም አቀፍ ሕግ ተጠያቂ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰላም የሚያደርገውን ጥረት አድንቀው ህወሓት ግን ለዚህ ጉዳይ ዝግጁነት የሌለው መሆኑን መረዳት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
አሸባሪ ቡድኑ አሁንም ትጥቅ ባልፈታበት ሁኔታ ለሰላማዊ ውይይት ዝግጁ ነኝ ማለቱ ተቀባይነት የለውም፤ ቡድኑም በባህሪው ለውይይት ዝግጁ ሆኖ እንደማያውቅ ገልጸዋል።