ውንብድና - የአሸባሪው ህወሃት የዕድሜ ልክ መገለጫ

23

የሰው ልጅ ለመኖር ከሚያስፈልጉት መሰረታዊ አቅርቦቶች መካከል ምግብ ቀዳሚው ሲሆን፣ ስናገኘው የእስትንፋሳችን ማስቀጠያ፣ ስናጣው የሌሎች ጥገኛና ተመጽዋች እንድንሆን ያደርገናል። በእጅ ሞልቶ የተትረፈረፈ ጊዜ ደግሞ በአንዳንድ ሀያላን እንደምናስተውለው ሌሎችን ለማንበርከኪያነት፣ ነጻነታቸውን ለመግፈፊያነት የሚጠቀሙበት የመታበያ መሳሪያ ሆኖ ያገለግላል፡፡ ለዚህም ነው የምግብ ጉዳይ የሉአላዊነት ጉዳይ ተደርጎ የሚወሰደው።

በምግብ እጦት የተጎዳ ሰው ህልውናውን ለማስቀጠል አድርግ የተባለውን ያደርጋል፤ ዝረፍ ካሉትም ይዘርፋል፤ ግደል ካሉትም ትዕዛዙን ለመፈጸም ወደ ኋላ አይመለሰም፡፡ በተለያዩ ዓለማት ለነፃነት እንታገላለን በማለት ጫካን መደበቂያቸው፣ ዝርፊያን መኖሪያቸው ያደረጉ አማፂያንና አሸባሪዎች የሚያሰልፏቸው ብኩን ነፍሶች የዘወትር ግብራቸው ሌብነትና ሌብነት ብቻ መሆኑን ያሳለፉት ታሪካቸው ይነግረናል፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ መሰል እውነታዎች ባይጠፉም በሌብነት ተወልዶ ከነሌብነቱ ከመንበረ ስልጣኑ የተባረረው አሸባሪው የህወሃት ቡድን በ27 ዓመት የአገዛዝ ቆይታው በዝርፊያ ባካበተው ሃብት ከአገር ጠል ተባባሪዎቹ ጋር በመሆን ሰላማዊ ዜጎችን እየገደለ፣ እያቆሰለ ከመኖሪያ ቀዬአቸው እያባረረ ለከፋ መከራ ዳርጓቸዋል አሁንም እየዳረጋቸው ይገኛል፡፡

አሸባሪው ህወሃት ከውልደቱ ጀምሮ አቅሙን ለማፈርጠም ሌብነትን ቀዳሚ ተግባሩ አድርጓል። ለእኩይ አላማው የሚያሰልፋቸውን ተዋጊዎች ያፈራው ደግሞ ለእርዳታ የተሰበሰበን እህል በመከልከልና ረሃብን እንደማስፈራሪያ መሳሪያ በመጠቀም መሆኑን ታሪኩ ያስረዳናል፡፡ አሸባሪ ቡድኑ የትጥቅ ትግል ላደርግ በረሃ ወርጄአለሁ ካለበት ቅጽበት አንስቶ የውንብድና ጉዞውን አሀዱ ብሎ የጀመረው ባንክ በመዝረፍ መሆኑን አመራሮቹ በኩራት ሲናገሩ በተደጋጋሚ አድምጠናቸዋል፡፡

ጫካ ወርዶ ከደርግ ጋር ሲዋጋ በነበረበት ወቅት በአገሪቱ ላይ የከፋ ረሃብ መከሰቱን ተከትሎ በተለይም በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በወሎና ትግራይ የሚገኙ ዜጎች ለጽኑ መከራ ተዳርገው ነበር፡፡ በዚሁ ወቅት ህልውናውን ለማስቀጠል ሲል ጫካ ለጫካ እየተሽሎከለከ ለትግራይ ህዝብ የተላከውን እህል ለተዋጊ መመልመያ፣ እንዲሁም እህሉን በመሸጥ የሚያገኘውን ገንዘብ ለመሳሪያ መግዣ እንዳዋለው ያለፈ ታሪኩን የሚያሳዩ ሰነዶች ይጠቁማሉ፡፡

በ1977 በነበረው ድርቅ ለተጎዱ የትግራይ ተወላጆች የመጣውን አልሚ ምግብ፣ አልባሳትና ድንኳኖች የወቅቱ ህወሃት አመራሮች ለጎረቤት አገር ነጋዴዎች ይሸጧቸው እንደነበር ቀደምት አባላቱ ማጋለጣቸውም አይዘነጋም፡፡ የቡድኑ አባል የነበሩት አቶ ገብረመድህን አርአያ የህወሃት አመራሮች የትግራይ ህዝብ እንደ ቅጠል ይረግፍ በነበረበት በ1979 አካባቢ ከድሃው ህዝብ ጎሮሮ በመሰወር እንዲበላሽ ያደረጉትን 45 ሺ ኩንታል እህል የተበላሸ እህል የሚጥል ኮሚሽን በማቋቋም ተከዜና ካዛ ወንዝ መጣላቸውን በቦታው ተገኝተው መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡

ነገሩ ተረት ቢመስልም በወቅቱ የቡድኑ አመራር የነበሩት አቶ ገብረመድህን በ1975 ዓ.ም ክርስቲ የምትባል አንዲት እንግሊዛዊት አጋራቸው ሶስት ሚሊዮን ዶላር ይዘው የመጡ እርዳታ ሰጪዎችን ለህወሃት አመራሮች ስታገናኛቸው በበላይ አመራሮች ትዕዛዝ ነጋዴ መስለው በመቅረብ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የመጣውን እህል መሸጣቸውን በመናገር ቡድኑ ረሃብን እንደ መሳሪያ መጠቀሙ የቀደመ ተግባሩ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

በተመሳሳይ አቶ ገብረመድህን “መሃመድ” በሚል መጠሪያ ሱዳናዊ ነጋዴ መስለው በመቅረብ 4 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት እህል በመሸጥ ለወያኔ አመራሮች ማስረከባቸውን በሰጡት ቃለ ምልልስ መናገራቸው ይታወሳል፡፡ በ1977 በተከሰተው አስከፊ ድርቅ ምዕራባውያን ድርጅቶች እና ለጋሾች ለእህል መግዣ የላኩትን ገንዘብ በህወሃት አመራሮች ትዕዛዝ ራሳቸውን በመደበቅና እህል ሻጭ መስለው በመቅረብ ጆንያውን ከላይ በእህል ከሥሩ ደግሞ በአሸዋ በመሙላት መሸጣቸውንም አረጋግጠዋል፡፡

የቀድሞ የህወሃት አመራር የነበሩት አረጋዊ በርሄ በበኩላቸው ይህንን ተግባር በተመለከተ “የዕርዳታ ሠራተኞቹ ተሞኝተው እንደነበርና በማጭበርበር ሂደቱ እስከ 100 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ገንዘብ መገኘቱን፣ ከዚህ ውስጥ 95 በመቶ የሚያክለው የጦር መሣሪያ ለመግዛት ወጪ መደረጉን መስክረዋል፡፡

“ነጻ አወጣዋለሁ” ያለውን ሕዝብ የዕርዳታ እህል እንዳይደርሰው በማድረግ አሰቃቂ በደል የፈጸመው አሸባሪው ህወሃት አሁንም በህዝቡ ላይ ተመሳሳይ ግፍ በመፈጸም ለህዝብ ምንም ቦታ የሌለው የሆድ አደሮች ስብስብ መሆኑን እያሳየ ነው። የእርዳታ እህል የሚያመላልሱ ተሽከርካሪዎችን ለጦርነት መጠቀም፣ ነዳጅ በመዝረፍ ህዝብ ርዳታ እንዳይደርሰው ማድረግ፣ የደረሰውን ርዳታም ከህዝብ ጉሮሮ እየነጠቀ በውድም በግድም ለመለመላቸው ተዋጊዎች ብቻ መስጠት መገለጫው ሆኗል።

አሸባሪ ቡድኑ ከበረሃ ህይወቱ አንስቶ የዘረፈውን የእርዳታ እህል፣ ገንዘብ እና ጥሬ ሃብት ለአመራሮቹ የግል ጥቅም በማዋል የትግራይን ህዝብ መነገጃ ሲያደርግ መቆየቱ አይዘነጋም::

“ሌባ ላመሉ ዳቦ ይልሳል” ይሉ ዘንዳ በተገንጣይ ስም እስከ አሁን ራሱን የሚጠራውና የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር ነኝ የሚለው ቡድን (አሸባሪው ህወሃት) ከውልደቱ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ በድሃ ደምና እምባ እየነገደ ነው፡፡

አሸባሪው ህወሃት የሰላም ጠበቃ ለመምሰል ጉንጭ አልፋ ጩኽቱን ከፍ አድርጎ ቢያሰማም ከቡድኑ እሳቤ የተወለዱት ግን ስደት፣ ዘረፋ፣ የምግብ እጥረት፣ ዘረኝነትና መሰል ቀውሶች ናቸው። አሸባሪው ህወሃት ከስልጣን ተባሮ መቀሌ ከመሸገ በኋላም ”ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ” በሌብነቱ ገፍቶበታል፡፡

በቅርቡም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ትግራይ ውስጥ ለሚያካሂደው የእርዳታ አቅርቦት የሚገለገልበትን 570 ሺህ ሊትር ነዳጅ ዘርፏል።

አሸባሪ ቡድኑ መቀሌ ከተማ ውስጥ በሚገኘው የዓለም ምግብ ድርጅት መጋዘን ውስጥ በሃይል በመግባት 12 ታንከሮችን ከ 570 ሺህ ሊትር ነዳጅ ጋር መዝረፉን የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ባስሌ በወቅቱ መናገራቸው ይታወሳል። የአሸባሪው ህወሓት ዘረፋ አስፀያፊና አሳፋሪ መሆኑንና ድርጊቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሰብአዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ወገኖችን ለከፋ አደጋ የሚያጋልጥ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት መሆኑን በአደባባይ መስክረዋል።

የቡድኑን የቀደመ ታሪክ የሚያውቁት አይዞህ ባዮቹ አሁን ላይ ፊታቸውን ያዞሩ በመምሰል ቡድኑ የዘረፈውን ነዳጅ በአስቸኳይ እንዲመልስም ጥሪ አቅርበዋል። ይሁንና ዊሊያም ዳቪድሰን የተባለው የአሸባሪው ህወሃት ደጋፊ በትዊተር ገጹ ባሰፈረው መረጃ ”ሕወሓት ለአለም ምግብ ድርጅት ያበደረውን ነዳጅ ነው የወሰደው ይሄም በማስረጃ የተረጋገጠ ነው” በሚል ያሰራጨው መረጃ አንዳንድ አካላት በፖለቲካ ተመራማሪ ስም ኢትዮጵይ ላይ ተቀምጠው ምን ያህል ሲያምሱን እንደኖሩ ያሳያል።

ዊሊያም ዳቪድሰን የኢትዮጵያ መንግስት በሕዳር 2013 ዓ.ም ከተሰጠው ፈቃድ ውጪ በሌላ ተልዕኮ ላይ መሰማራቱን በማረጋገጡ አገሪቷን ለቆ እንዲወጣ ማድረጉ ይታወሳል።

አሸባሪው ሕወሓት በአማራ ክልል የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት መጋዘን ላይ ዘረፋ መፈጸሙን የእርዳታ ድርጅቱ ባወገዘበት ወቅት በተመሳሳይ ማርቲን ፕላውት የተባለው የህወሃት አፈቀላጤ “ይህን ጉዳይ ዘረፋ አልለውም ምክንያቱም እየተካሄደ ያለው ጦርነት ነው በጦርነት ውስጥ ደግሞ ረሃብ አለ” በማለት የውጭ ኃይሎችን አይዞህ ባይነት በግልጽ አሳይቷል፡፡

ማርቲን ፕላውት የቢቢሲ ጋዜጠኛ ሳለ እ.አ.አ በ2010 በሰራው ዘገባ አሸባሪው ህወሃት በ1977 ዓ.ም በተከሰተው ድርቅ ለትግራይ ተረጂዎች የሚላከውን እርዳታ በመሸጥ ለጦር መሳሪያ ግዢ ሲያውል እንደነበርና በወቅቱ ለመሳሪያ ግዢ ቡድኑ ከ95 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማውጣቱን በመዘገብ የዶክተር አረጋዊ በርሄን ማስረጃ ማጠናከሩ አይዘነጋም።

አሁን ላይ ደግሞ ማርቲን ፕላውት አሸባሪውን ህወሃት ለትግራይ ሕዝብ የሚገባውን እርዳታ ለጦርነት ሲያውል የተግባሩ ደጋፊ በመሆን መሰለፉን ለተመለከተ ህወሃትን ከኋላ ሆኖ የሚገፋው ማን እንደሆነ ለመረዳት አያዳግትም።

ከላይ የተመለከትናቸው ሃቆች እንዳሉ ሆነው ህወሃት በአፈቀላጤዎቹ በኩል የሚያሰማው ቀረርቶ በመከራ ውስጥ የሚዳክሩትን የህጻናት፣ ሴቶችንና አረጋዊያን ለተጨማሪ ችግር የሚዳርግ የስግብግብነት ጥግ ማሳያ ስብስብ መሆኑን የሚያጋልጡ ናቸው።

አሸባሪው ቡድን ከሰብዓዊነት ባፈነገጠ መልኩ ከህዝብ ጉሮሮ ላይ በመንጠቅ የፈጸመውን ዘረፋ መንግስት ለክልሉ ህዝብ የሚያደርገውን ድጋፍ መና የሚያስቀር ድርጊት በመሆኑ አለም አቀፍ ማህበረሰቡ እንዲያወግዘውና መላ እንዲያበጅለት ቢያሳውቅም ያገኘው ምላሽ ግን በተገቢው ልክ አይደለም፡፡

አሁንም ለቡድኑ አንቀልባ በመዘርጋት እሹሩሩ የሚሉት የውጭ ኃይሎች ድርጊቱ ግልጽ የጦር ወንጀልና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ ህግጋትን የጣሰ መሆኑን በማሳወቅ ከጥፋቱ ካላስቆሙት አሸባሪው ህወሃት ከዚህ የከፋ ነገር መፈጸሙ እንደማይቀር ሊረዱት ይገባል።

ቡድኑ ከፈጸመው ዝርፊያ ባሻገር ድርጊቱን ለማስቆም የሞከሩ የሰብአዊ እርዳታ ባለሙያዎችን ማሰሩን ለተመለከተ ህወሃት በሌብነት ተወልዶ በሌብነት ለመሞት መቁረጡን ይረዳል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ባወጣው ሪፖርት አሸባሪው ህወሃት በወረራ  በቆየባቸው የአፋር እና የአማራ ክልል አካባቢዎች የግል ንብረቶች እና የመንግሥት ተቋማት ላይ መጠነ ሰፊ ዘረፋ እና ውድመት መፈጸሙን አስታውቋል፡፡

በተለይም የጦር ወንጀልን እና በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ላይ የሚካተተውን ለሲቪል ሰዎች ሕልውና አስፈላጊ የሆኑ የማሳ ሰብሎች፣ የምግብ እህሎች፣ የቤት እንስሳትን ማውደሙንና መዝረፉንም አረጋግጧል፡፡

ከዚህ ባለፈ ትውልድን በመግደልና በማምከን ተወዳዳሪ የሌለው የአሸባሪው ህወሃት አመራር ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት እና የመንግሥት ድርጅቶች ላይ በማነጣጠር ስልታዊ በሆነ መንገድ  የዘረፋ እና የማውደም ተግባር መፈጸሙን አጋልጧል።

በአጠቃላይ የአሸባሪው ሕወሓት አፈ-ቀላጤዎች፣ አይዞህ ባዮችና ጀሌዎች ለቡድኑ ጥብቅና በመቆም የሚያሰሙት የሀሰት ጩኽት ከኢትዮጵያ እውነት ገዝፎ እንዳይታይ በጋራ መስራት ይገባል። አሸባሪው ቡድን በዜጎች ችግርና ስቃይ ጥቅሙን ማስከበር ከምስረታው ጀምሮ ሲጋተው የኖረ ባህሪው መሆኑን ለወዳጅም ለጠላትም ማሳወቅ ያሻል።

አሸባሪው ህወሃት ለሀገርና ለዜጎቿ ምንም ቦታ የሌለው መሆኑን በቅርቡ የተጋለጠው የቡድኑ ሰነድ ፍንትው አድርጎ አሳይቷል። አገር ተስፋዋን እየጨበጠች ያለችበትን ግብርና በተለይም የስንዴ ምርት ለማጨናገፍ በሰነድ አስደግፎ ከመስራት የበለጠ አገር ጠልነት የለም። ከዚህ በላይም በህዝብ መጨከን የለም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በአንድ ወቅት ስለአሸባሪ ቡድኑ ስግብግብነት ሲገልጹ በአፉ አጥንት ይዞ ውሀ ዳር በቆመ ውሻ መስለውት ነበር።  እውነትም ቡድኑ የራሱን ጥላ እያየ ሲጮህ የአፉን የሚጥል ስግብግብ ነው።

ኢትዮጵያውያን ይህን ተገንዝበው በአንድ እጃቸው ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ልማታቸውን በማስቀጠል በሌላ እጃቸው አገርና ልማቷን ለማዳከም የሌብነትና የጥፋት መረባቸውን ዘርግተው እንደ ውሻው የሚጮሁ አካላትን ሴራ መበጣጠስ ይገባቸዋል።

የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በሁለቱ ምክር ቤቶች መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ ከሁሉም ነገር በፊት ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት እንደምትሰራና ጉዞዋን ለመግታት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ መከላከልን መሰረት ያደረገ የማስታገሻ ርምጃ እንደምትወስድ አስረግጠው ተናግረዋል።

ኢትዮጵያዊያንም በዚሁ አገራዊ አቅጣጫ መሰረት ሰላምን፣ ልማትን በማስቀደም የኢትዮጵያን ከፍታ እያረጋገጡ ይህን ለማደናቀፍ የሚደረጉ ማናቸውንም ጥረቶች በጋራ መመከት ይገባቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም