ቀጥታ፡

አየር መንገዱ ለ17 ዓመታት የተገለገለበትን የመንገደኞች አውሮፕላን ወደ ተሟላ የጭነት አገልግሎት ቀይሮ ስራ አስጀመረ

ጥቅምት 02 ቀን 2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ለ17 ዓመታት የተገለገለበትን አንድ የመንገደኞች አውሮፕላን ወደ ተሟላ የጭነት አገልግሎት ቀይሮ በዛሬው እለት ስራ አስጀምሯል።

በስራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ፣ በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አቶ አለልኝ አድማሱ፣ የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።

አየር መንገዱ የመንገደኞች አውሮፕላኑን  ሙሉ በሙሉ ወደ እቃ ጫኝነት ቀይሮ ስራ ላይ ሲያውል በአፍሪካ የመጀመሪያ መሆኑ ተገልጿል።

ይህ ለአፍሪካ አቪየሽን ኢንዱስትሪ አዲስ ጅማሮ መሆኑ ተጠቁሟል።

በዚህ ወቅት ለመገናኛ ብዙሃን ማብራሪያ የሰጡት የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው፤ ከዚህ ቀደም 25 የሚሆኑ አውሮፕላኖች በጊዜያዊነት ወደ ጭነት አገልግሎት ተቀይረው ነበር ብለዋል።

ይህ ስራ አውሮፕላን ውስጥ የነበሩ የመቀመጫ ወንበሮችን ብቻ በማውጣት በጊዜያዊነት ለጭነት አገልግሎት እንዲውሉ የማድረግ ስራ የነበረ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይሁን እንጂ የአሁኑ ሂደት የመንገደኞች አውሮፕላኑን ሙሉ ለሙሉ በመቀየር በቋሚነት ለጭነት አገልግሎት ብቻ እንዲውል የማስቻል ስራ ነው የተከናወነው ብለዋል።

አውሮፕላኑን ወደ ጭነት አገልግሎት ለመቀየር አምስት ወራት እንደወሰደ እና አውሮፕላኑ አሁን ላይ 60 ቶን ጭነት ይዞ የመብረር አቅም እንዳለው ተናግረዋል።

የመንገደኞች አውሮፕላኑን ወደ ጭነት አገልግሎት ሰጪነት ለመቀየር 14 ሚሊዮን ዶላር ገደማ እንደወሰደ ጠቅሰው፤ ከውጭ አዲስ የጭነት አውሮፕላን ለመግዛት ግን 80 ሚሊዮን ዶላር እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።

አሁን ተቀይሮ ወደ ስራ እንዲገባ የተደረገው አውሮፕላን አየር መንገዱ ለ17 ዓመታት የተገለገለበት መሆኑን በማንሳት፤ይህም በኢንዱስትሪው ያለ አሰራር መሆኑን ተናግረዋል።

የመንገደኞች አውሮፕላኑን ወደ ጭነት አገልግሎት ለመቀየር በዘርፉ ዓለም አቀፍ ልምድ ካለው አይ ኤ አይ ከተሰኘ የእስራኤል ኩባንያ ጋር በጥምረት መሰራቱንም አንስተዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የጭነት አገልግሎት የሚሰጡ አውሮፕላኖች እጥረት በመኖሩ፤ ወደ ዕቃ ጫኝ የተቀየረው አውሮፕላን የአየር መንገዱን የጭነት አገልግሎት እንዲያሳድግ ይረዳዋል ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አቶ አለልኝ አድማሱ በበኩላቸው አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና ብቻ ሳትሆን የጠቅላላ አፍሪካ ሀገራት የመንገደኞች አውሮፕላን ወደ ጭነት መቀየሪያ ማዕከል ትሆናለች ብለዋል።

ይህን እውን ለማድረግ ጠንክሮና ተግቶ መስራት እንደሚገባ ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም