የፈተና ደንብን በተላለፉ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ላይ ተጣርቶ በሚቀርበው ማስረጃ መሰረት ፈተና እስከመሰረዝ የሚደርሱ እርምጃዎች ይወሰዳሉ-ትምህርት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የፈተና ደንብን በተላለፉ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ላይ ተጣርቶ በሚቀርበው ማስረጃ መሰረት ፈተና እስከመሰረዝ የሚደርሱ እርምጃዎች ይወሰዳሉ-ትምህርት ሚኒስቴር
ጥቅምት 2/2015/ኢዜአ/ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የደንብ መተላለፍ በፈጸሙ ተማሪዎች ላይ ተጣርቶ በሚቀርበው ማስረጃ መሰረት ፈተና እስከመሰረዝ የሚደርሱ እርምጃዎች እንደሚወስድ የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ ለመጀመሪያ ጊዜ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የተሰጠው የ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል የመጀመሪያ ዙር የማህበራዊ ሳይንስ ብሔራዊ ፈተና መጠናቀቁን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።
በዚህም በመጀመሪያው ዙር ለፈተና ከተመዘገቡ 595 ሺህ 700 ተማሪዎች ውስጥ 586 ሺህ 541 ተማሪዎች ለፈተና መቅረባቸውን የትምህርት ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አመለወርቅ ሕዝቅኤል ገልጸዋል።
በዩኒቨርሲቲ ውስጥ የመፈተን ተሞክሮው የመጀመሪያ እንደመሆኑ መጠን የፈተና ሂደቱ ላይ ብዙ ችግሮች ሊከሰቱ እንደሚችል ቢገመትም፤ ፈተናው በአብዛኞቹ መፈተኛ ጣቢያዎች በመልካም ሁኔታ መጠናቀቁን ጠቅሰዋል።
በመጀመሪያው የፈተና ቀን (መስከረም 30/2015 ዓ.ም) በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በደረሰው የድልድይ መደርመስ አደጋ የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፍ ከአራት መቶ በላይ ተማሪዎች ላይ ቀላልና መካከለኛ ጉዳት መድረሱ ተገልጿል።
በተከሰተው ሁኔታ የትምህርት ማህበረሰቡ ማዘኑን ገልጸው፤ በአደጋው ምክንያት ፈተና ያልወሰዱ ተማሪዎች ፈተናውን በሁለተኛ ዙር እንደሚወስዱ ተናግረዋል።
ከዚህ ውጭ በተወሰኑ የፈተና ማዕከላት ከስርዓት ባፈነገጠ መንገድ ፈተና አንፈተንም ብለው የወጡ ተማሪዎች ስለመኖራቸውም ተመላክቷል።
ለአብነትም መቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ መካነ ሰላም ካምፓስ፣ ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ፣ ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ እና ደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ችግሮቹ የታየባቸው መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ተፈታኞች ኃይል የተሞላበት ሁከት በመፍጠር የአንድ ተማሪ ህይወት ማለፉን እና በፈተና አስፈጻሚዎች እና በጸጥታ ኃይሎች ላይ ጉዳት መድረሱን ነው የተናገሩት።
በተጨማሪም በመፈተኛ ክፍሎች በቡድን ወይም በግል ደንብ የተላለፉ ተማሪዎች መኖራቸውን የሚያመላክቱ መረጃዎች መኖራቸውን አነስተው፤ ይህንንም በማስረጃ በማስደገፍ ጥሰት መፈጸማቸው የተረጋገጠባቸው ተማሪዎች ላይ ፈተና እስከመሰረዝ የሚደርስ እርምጃ እንደሚወሰድ ጠቁመዋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው፤ በደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ፈተናውን የማወክ ተግባር መፈጸሙን ገልጸዋል።
የአካባቢውን የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም የሃይማኖት አባቶች በማስተባበር ፈተና ለመፈተን ፍላጎት የነበራቸው ከሰባት ሺህ በላይ ተማሪዎች ተመልሰው ገብተው ፈተናውን እንዲያጠናቅቁ መደረጉን ጠቁመዋል።
ትምህርት ሚኒስቴር ለፈተናው በስኬት መጠናቀቅ አስተዋጽኦ ለነበራቸው አካላት ምስጋና አቅርቧል።